#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት ትግል በሚያካሂድበት ወቅት ለጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ይቅርታ ጠየቀ።

ፓርቲው ከለውጡ በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።

በዓመታዊ ጉባኤው መክፈቻ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ወይዘሮ ቆንጂት ብርሃን እንዳሉት፤ ኢህአፓ በትግል ወቅት በነበረው አስገዳጅ ሁኔታ የሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በመሆኑም ለተሰራው ስህተትና ለጠፋው የሰው ህይወትም ሆነ ንብረት ፓርቲው ይቅርታ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብን በተለይም ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦችና ግለሰቦች ዛሬ በጉባኤው በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

ቀድሞ የተሰራው ስህተት አሁን ላለው ትውልድ ትምህርት እንዲሆንና በየቀኑ በተለያዩ አካላት የሚፈጸሙ ስህተቶች እንዲታረሙ የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

ኢህአፓ በ1964 ዓ.ም ከተመሰረተ ወዲህ ለአርሶ አደሩ የመሬት ባለቤትነት ለብሔር ብሔረሶችና ለሴቶች እኩልነት እንዲሁም ለሌሎችም መብቶች መረጋገጥ ለዘመናት ሲታገል መቆየቱን አስታውሰዋል።

በቀጣይ ፓርቲው የመንግስት ጉድለቶችን ለማረም፣ የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ፣ የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥ አበክሮ እንደሚሰራ ሊቀመንበሯ ገልጸዋል።

በቀጣይ ፓርቲው ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለመንቀሳቀስ እየሰራ እንደሆነም አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከአቻ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ሊቀ መንበሯ ለኢዜአ ተናግረዋል።

”ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የፓርቲው ጉባኤ አዳዲስ የፓርቲ አመራሮች ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫ ይቀመጣል” ብለዋል።

ኢህአፓ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ያለው ሲሆን በ1966 ዓ.ም በአገሪቱ አብዮት መፈንዳቱን ተከትሎ የመንግስት ስልጣንን ከተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት ‘ደርግ’ ጋር መግባባት አለመቻሉን ተከትሎ ብዙ ችግሮች ሊደርሱ መቻላቸው ይታወሳል።

በዚህ አለመግባባት የተነሳም በርካታ ወጣት ምሁራን ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል። ብዙዎቹም ለእስር፣ ለአካል ጉዳትና ለስደት ተዳርገዋል።

(ENA)

Report Page