#ETH

#ETH


‹‹ኢትዮጵያን ለመፍረስ የሚዳርጋት ስጋት የለም›› - ጀነራል ብርሃኑ ጁላ :- ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም

አዲስ አበባ፡- በሀገራችን ውስጥ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከጀርባ ባሉ ስውር እጆች በሚደገፉ ኃይሎች ወይንም ቡድኖች የሚፈጠሩ ግጭቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እያለ ኢትዮጵያን የሚበታትን እና ለመፍረስ የሚዳርጋት ስጋት እንደሌለ ተገለጸ፡፡

የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ፖለቲከኞች የሚሉትን ሊሉ ይችላሉ፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል የት ሄዶ ነው ኢትዮጵያ የምትፈርሰው? ኢትዮጵያን የሚበታትንና ለመፍረስ የሚዳርጋትም ምንም አይነት ስጋት የለም፡፡

እንደ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ገለጻ፣ አሁን በተጨባጭ በሚታየው ሁኔታ ሀገራችን የዳር ድንበር መደፈርና የውጭ ስጋት የለባትም፡፡ በሰሜን፣ በምስራቅ፣ በደቡብ፣ በምእራብ ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም ሰላማዊ ነው፡፡ ሕዝቡ ተረጋግቶና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ትብብርና ድጋፉን አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል:: በአጠቃላይ ህዝቡ ሊሸበር አይገባውም፤ በመረጋጋት ሥራውን መስራት አለበትም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ሲፈጠሩ ሰላም ለማስፈን የሚገባው የተፈጠረው ችግር ከአካባቢው ፖሊስ፤ ከፌዴራል ፖሊስና ከአካባቢው ልዩ ኃይል አቅም በላይ ሲሆንና ግልጽ ትእዛዝ ሲሰጠው ብቻ ነው ያሉት ጀነራል ብርሃኑ፣የመከላከያ ተልእኮና ግዳጅ የተለየ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በባሕርዳር፤ በከሚሴ፤ በሃዋሳ/ሲዳማ፣ በሶማሌ፤ በጉጂ የተፈጠረው አይነት ችግር ሲያጋጥም፤ መከላከያ ገብቶና ከፌዴራል ፖሊስና ከክልል የጸጥታ ኃይል ጋር ተጋግዞ በመስራት በጋራ የፈታቸው ችግሮች አሉ ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

ከለውጡ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ጥያቄዎችን ሽፋን እያደረጉ በስውርና ከጀርባ ባሉ እጆች የሚፈጠሩ ግጭቶች በተደጋጋሚ ታይተዋል፤ አሁንም አሉ ያሉት ጀነራል ብርሃኑ፣ በየቦታው የሚታዩት የሰላም መደፍረሶች ከጀርባቸው ገፊ ኃይልና እጅ እንዳላቸውም ይታመናል ብለዋል፡፡

በጥምረትና በቅንጅት እየተናበበ የሚሰራው የሀገሪቱ የጸጥታ ኃይል ሀገርንና ሕዝብን ከአደጋ የመጠበቅና የመከላከል ግዳጁን እንደሚወጣ ጠቅሰው፣ ሀገራችን የራሷን የውስጥ ደህንነት ከመቆጣጠር አንጻር ችግር የለባትም ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ጋዜጣ)

Report Page