#ETH

#ETH


የፀረ ሽብርተኝነት ህጉ አገሪቱ ከጀመረችው ለውጥ ጋር አብሮ የማይሄድና አፋኝ ህግ በመሆኑ ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሊያደርገው እንደማይገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ።

በወንጀል የተጠረጠሩ ዜጎችን መደበኛ ህጉ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ መሰረት እየተጠቀሙ መመርመር እየተቻለ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ “የምርምራ ጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ተገቢ አይደለም” በማለት ነው ኮሚሽኑ የሚገልጸው።

ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ‘የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር’ በሚል የወጣው “የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001” በርካታ ዜጎችን የሚጨቁን፣ ለእንግልት የሚዳርግ መሆኑን በመግለጽ ይቃወሙታል።

ዜጎች በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ አማካኝነት በሽብር ተከሰው ለእስር፣ እንግልት ጭቆና ሲዳረጉ መቆየታቸው በተደጋጋሚ መግለጻቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት፤ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ መንግስት ዜጎችን የሚጨቁንበት መሳሪያ አድርጎት እንደነበር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጻቸው ይታወሳል።

አያይዘውም እስካሁን ‘ዜጎች ሳይሆኑ አሸባሪ የነበረው መንግስት ነው፤ ለዚህም ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ከዚህ በኋላም ተግባራዊ አይደረግም’ በማለት ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።

በአሁኑ ወቅት የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ በመሻሻል ሂደት ላይ እያለ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ለመመርመር የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሲያደርገው ይታያል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ለኢዜአ እንዳገለጹት፤ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ከኢትዮጵያ ለውጥ ጋር የማይሄድ ነው።

የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ የተወገዘ፣ የተነቀፈና መሻሻል እንዳለበት ታምኖበት በመሻሻል ሂደት ላይ ያለ ህግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ህጉ ሙሉ በሙሉ የተሻረ ባይሆንም እንኳ በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የፖለቲካ መነቃቃት ጋር አብሮ ስለማይሄድ “ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ መሆን የለበትም” ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ለክስ መመስረቻ ሆኖ ያለማገልገሉን ጠቁመው፤ ነገር ግን ፖሊስና ዐቃቤ ህግ ለምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ሲያደርጉት መስተዋሉን ነው ያብራሩት።።

በመሆኑም ፖሊስና ዐቃቢ ህግ በወንጀል የጠረጠሯቸውና በቂ መረጃ የሚያቀርቡባቸውን ሰዎች የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ያለባቸው በመደበኛው ህግ መሆን እንደለበት ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ የሚሻረው በምክር ቤቱ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ አዋጁ በሌላ አዋጅ እስካልተቀየረ ወይም ባጸደቀው አካል እስካልተሻረ ድረስ “ጥቅም ላይ መዋሉ አይቀርም” ብለዋል።

የጸረ ሽብርተኝነት ህጉ ዜጎችን የሚጨቁንና አፋኝ በመሆኑ የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ተሻሽሎ በረቂቅ ደረጃ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

እየተሻሻለ ያለው የጸረ ሽብርተሽነት ህግ ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ለህዝብ ተወካዮች ቀርቧል፤ ‘በቅርቡ ሲጸድቅ ስራ ላይ ይውላል’ ብለዋል።

(ENA)

Report Page