#ETH

#ETH


“ለራሴ ብሔር ማለት ከበዛ አገር ለምኔ የሚል ነገር ይመጣል፤ ሁለቱን ሚዛናዊ አድርጎ መሄድ ላይ ክፍተት ነበር” ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

• አመራሩ ብሔሩን እየለየ የሚያገለግል ከሆነ አስቸጋሪ ነው። በእያንዳንዱ ክልል የተለያየ ብሔር ብሔረሰብ አለ።

መንግሥት እኩል ካላገለገለ አድሎ ከተፈፀመ በአግባቡ አልተገለገልኩም የሚል ጥያቄ ያቀርባል።

• አንዱ ከአንዱ ጋር የሚገፋፋ ከሆነ አንድነት አይመጣም። ሰው ሲሞት ለምን ሞተ ከማለት ይልቅ የየትኛው ብሔር ተወላጅ ብዙ ሞተ እየተባለ ነው። ይህ ቀድሞ መሠራት የነበረበት ሥራ ባለመሥራቱ የመጣ ነው።

• ማንኛውም ሰው የራሱን ማንነት እንዲከበርለት የሚፈልግ ከሆነ የሌላውንም እኩል ማክበር አለበት። እዚህ ላይ ትልቅ ክፍተት ነበር።

• ስለብሔር ማሰብ ላይ ብቻ መተኮር የለበትም። አንዲት ትልቅ አገር መኖሯንም መዘንጋት የለበትም።

• አገርን ከመገንባት ለሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል ክብር እና እውቅና መስጠት ያስፈልጋል።

• ብሔራዊ ማንነት ቢኖረንም ከአገራዊ ማንነት ውጭ መሆን አንችልም። እርስ በእርሳችን እንከባበር የምንለው አገራችንን ለመገንባት ነው።

• ትልቁ ችግር አገራዊ እና ብሔራዊ ማንነት ሚዛናቸውን ጠብቆ አለመሄዳቸው ነው። ለራስ ብሔር ብቻ ማሰብ ትርጉም የለውም።

• ወደ ውድድር ከተሄደ ሌላ ፅንፍ ይመጣል። ስለዚህ አንዱ ለአንዱ ብሔር የሚወዳደርበት ሳይሆን የሚተዋወቅበት፤ አንዱ ካለ አንዱ መኖር እንደማይችል የሚታወቅበት መድረክ ነው።

• ባህልንና ታሪክን በማጣቀስ የሌላው ከኔ ይጎላል ከማለት ይልቅ እኔም ባህል አለኝ ሌላውም አለው በማለት፤ የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌላውንም አስቦ ከማዋል አንፃር ችግር አለ።

• የሕገ መንግሥቱም የመጨረሻ ግብ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር ነው። ሁሉም የየራሱን ድንበር ከልሎ ስለራሱ ብቻ እንዲያስብ አይደለም።

• አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር ሐሳቡን በሁሉም ውስጥ ማስረፅ ላይ ክፍተት አለ። ነፃነት ያለገደብ ቢሰጥም ሕገ መንግሥትና ሕጎች ምን ይላሉ? በሕግ ገደብ የለም ወይ? መብት ሲታሰብ ግዴታስ ምንድን ነው? እነዚህን ማሳወቅ ላይ ክፍተት ነበር።

• ወጣቱ ትውልድ በስሜት ሳይሆን በስሌት እንዲመዝን ከተፈለገ ሕገ መንግሥቱን ማሳወቅ እና የራሱን አቋም እንዲወስድ ማድረግ ያስፈልጋል።

• ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ የተሠሩ ሥራዎች በተለይ ወጣቱ ላይ ከመሥራት አንፃር ክፍተት ነበር። እነዚህ ክፍተቶች ምክር ቤቱ ላይ ነበሩ።

• ሰው መብቱን እንዲያውቅ ከተደረገ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል። መልስ ከሌለ ወደ ግጭት የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል።

• ችግሩ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ሳይሆን አፈፃፀም ላይ ያለው ችግር ነው። አመራሩ እኩል ከማስተናገድ አንፃር ያለው ክፍተት ነው ወደ ግጭት እያመራ ያለው።

• ዘንድሮ ከተመደበልንን በጀት አብዛኛው በፊት ከሚደረገው በተለየ መንገድ ማሸብረቅ ላይ ሳይሆን የዜጎች አመለካከትን መገንባት ላይ አውለነዋል።

• አመለካከት ካልተቀየረ ትናንት የተሠራው በአምስትና በአስር ደቂቃ ስለሚጠፋ ትርጉም የለውም። ስለዚህ በዚህም በዛም በተለያዩ ምክንያቶች በህዝቦች መካከል መቃቃር ተፈጥሯል።

• በጀቱን ይሄን መቃቃር በባህላዊ እና ዘመናዊ መንገድ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲቀር መረጋጋት እንዲፈጠር እና ግጭቱ እንዲቀዛቀዝ መሥራት ላይ አውለነዋል።

• የፌዴራልና የክልል መንግሥታት፤ የክልል መንግሥታትና የክልል መንግሥታት ግንኙነት የሕግ ማዕቀፍ የለውም።

• የዩኒቨርሲቲ ወጣቶች ሌላ ሃይል ሳይዛቸው ቀድሞ ቢያዙ ኖሮ የተፈጠረው ችግር አይመጣም ነበር። ወጣቶች ብዝሃነታቸውን አክብረው እንዲኖሩ አሁን ያለው ግጭት እንዲቀንስ ይሠራል።

• የዴሞክራሲ ተቋማት ሥራ ተበታትነው መሥራታቸው ውጤት የማያመጣ በመሆኑ እነርሱንም በማቀናጀት ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር ይሠራል።

• ሌላው ግጭት ከመፈጠሩ በፊት ጥናት አካሂዶ የመከላከያ ስትራቴጂ የለም። ይህን ለመሥራት ቢጀመርም የተወሰነ ነገር ይቀራል። ከተፈጠረ በኋላ ዕሳት ማጥፋት ሳይሆን ቀድሞ ለመከላከል እየተሠራ ነው።

• ልዩነትን የሚያጎሉ አመለካከቶች ሲኖሩ በተጠና መንገድ ይህን በሚፈታ መንገድ ከተሠራ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ለአንድነት ጠቃሚ ነው። ዓመትን ጠብቆ የሚሠራ ሳይሆን ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ መሆን ነበረበት።

ምንጭ፦ አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም

Report Page