#ETH

#ETH


የአ/አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑና በፀረ-ሽብር አዋጅ ተከሰው በእስር ያሳለፉ አካላት መንግስት ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲሰጥ፣ ካልሆነ መንግስትን በዓለም አቀፍ ሕግና በሌሎች ፖለቲካዊ አማራጮች እንደሚጠይቁ ገለፁ።

ህዳር 25-2012 ሓሙስ

የአ/አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ፣ በአፋኙ የፀረ-ሽብር ሕግ ሰለባ የነበሩ አካላት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል። የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው።፦

ከአ/አበባ ፀረ-ሽብር ሰለባዎች ማህበር የተሰጠ

ጋዜጣዊ መግለጫ !


ለፍትህ ታግለናል፤ ለፍትህ እንኖራለን!!!


እኛ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆንን ባለፉት 27 ዓመታት በህወሓት-ኢህአዴግ መንግስት በፖለቲካ አመለካከታችንን ምክንያት በተፈጸመብን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የከፋ ግፍ ሞራላችንን ሰብአዊ ክብራችን ተደፍሮና አካላችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስመልክቶ ጥር 25 ቀን 2011 በሽብር ክስ የተወነጀልን በቁጥር 300 የምንደርስ የፖለቲካ እስረኞች ከአ/አበባ ከተማ መስተዳደር ም/ከንቲባ ጋር በካፒታል ሆቴል በነበርን ውይይት ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበን ከከተማው ከንቲባ በኩልም የተሰጡን ምላሽ እንደነበረ ይታወቃል ፡፡በመሆኑም የሚዲያ ቤተሰቦች፣ አድማጭ ተመልካቾች ቃል የተገቡልንን ከሲዲ ቪዲዮ ላይ መከታተል የምትችሉ ይሆናል ፡፡

ከሁሉ በፊት በሀገራችን ኢትዮጵያ ማንንም በማይወክሉ ተራ ሌቦችና ከፋፋይ ቡድኖች እጅ ወድቃ በነበረበት ወቅት የአዲስ አበባ ሀብት በእብሪትና በማን አለብኝነት በሚዘረፍበት ወቅት አምባገነኑን የኤህዴግ መንግስት በአደባባይ በመቃወምና በምርጫ ካርድ አታስፈልጉንም በማለት በማህበራዊ ትስስር ሚዲያዎች እና በሌሎች ሚዲያዎች በመሞገት በግልጽ ባደረግነው ትግል ባልሞ ተኳሾች የተገደሉ፣ የተሰደዱ፣ የተፈናቀሉ፤ በአደባባይ የተረሸኑና እስከ ዛሬ የት እንደደረሱ የማይታወቁ፤ ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከየስራ ገበታቸው የተሰወሩ እና ከየጎዳናው እየተያዙ ብዙ ሺዎችን በጅምላ አፈሳ በተለያዩ ወታደራዊ ካምፖችን በማጋዝ ኢ-ሰብአዊእና ዘግናኝ ግፍ በመፈጸም በአዲስ አበባ እና በመላው ሀገራችን ዜጎች ላይ የተካሄደውን የጭካኔ ተግባራትን ታሪክ የሚዘነጋቸው አይደሉም ፡፡

እኛ በዚህ ማህበር የተሰባሰብነውና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያልተቀላቀሉንም ሆኑ በሞት የተለዩን በአረመኔዎቹ ግፍና በባለሰልጣናት ርኀራሄ የለሽ እርምጃ እና በቃላት ለመግለጽ የሚዘገንኑ ስቃዮች ያሳለፍንባቸው አመታትን ስናስብ ቂም እና በቀልን ሳይሆን ይቅር ባይነትን፣ የሀገር ሰላምን በማስቀደም የተበዳዮችን ብቻ ሳይሆን የበዳዮችንም ነጻነት የሚያረጋግጥና ለሁላችንም የሚበጅ ስርአት እንዲመሰረት ቆራጥ ግን ከባድና እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈለግ ቆርጠን መነሳታችንን በተግባር አሳይተን ለዛሬ ደርሰናል ፡፡

እንደሚታወቀው ላለፉት ለ14 ወራት በማህበር ደረጃ ተደራጅተን የተለያዩ ጥያቄዎቻችንን ለመንግስት ያቀረብን ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የጸረ-ሽብር አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በግፍ ሰቅጣጭ ዋጋ የከፈሉ ግን በህይወት የተረፉት አምና ጥር 25 ቀን 2011 በካፒታል ሆቴል በተደረገው ስብሰባ ባቀረብነው ጥያቄ የከተማው መስተዳድር ብዙ ብዙ ቃል ገብተው ነበር፤ ቃል በገቡበት ወቅት ያስተላለፉት መለዕክት፦ "ይህን የመሰለ ስቃይ በእናንተ ያበቃ ዘንድ በርትተን በመሥራት እናንተን እናቋቁማለን" ብሎ ከሸነገሉን በኃላ ማእከላዊን የመሰለ የስቃይ ጎሬ ቀለም ከመቀባትና ሙዚየም ከማድረግ ያለፈ ለአመታት በዚያ ቤት ንጹኃን ዜጎች አካላቸው የጎደለ፣ ቤት ንብረታቸው የተበተነ፣ ልጆቻቸው እና ወላጆቻቸው ያለጠዋሪና ረዳት የቀሩባቸውን ሰለባዎች መዘንጋት ክፉኛ አሳዝኖናል፡፡ እኛ የህወሓት ኢህአዴግ የጸረ- ሽብር ህጉ ሰለባዎች ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ለመንግስት አካላት ቀላልና ምንም የማይከብዱ፣ የሀገርን ጥቅምና ህልውና የማይፈታትኑ ናቸው ከማለት ባሻገር እስከ ዛሬ ነገሮችን ከማወሳሰብ ውጭ ጠብ የሚል ነገር አልታየም ፡፡ እነዚህ ለዛሬው ለውጥ ብልጭታ ቢያንስ አስተዋጽኦ አላቸው እና የትም ወድቀውና አስታዋሽ አጥተው ሲቀሩ ማየት ከዛኛው በደል የከፋ ቢሆን እንጂ ያነሰ አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የገባውን ቃል የማያከብር መንግስት ከመባል የሚያድን አይሆንም፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ ጥር 25 ቀን 2011 በካፒታል ሆቴል በነበረን ስብሰባ የገቡትን ቃል አምነን ላለፉት 11 ወራት ምላሻቸውን በትዕግስት የጠበቅን ሲሆን በእነዚህ ጊዜያቶች የእስረኞቹ ኮሚቴ በከንቲባው ቢሮ ብቻ የተመላለሰው ከበቂ በላይ መሆኑ ህዝብ እንዲያውቅልንና ሰብአዊ መብታችን የሆነውን ጉዳይ ለማስፈጸም እና ሀገሪቱ የተቀበለቻቸውን አለም አቀፍ ህጎችን ተንተርሰን የሀገራችን ህገ መንግስት በሚፈቅድልን መሰረት ትግላችንን የምንቀጥል መሆኑን የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልንና "ማንኛውም ሰው! የሰብአዊ ፍጡር እንደ መሆኑ መጠን የማይገሰስ በሰላም የመኖር የአካል ደህንነት የመጠበቅና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብት አለው" የሚለውን ጨምሮ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብታችን በመግፈፍ፤ ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ ክብራችንን በሚያዋርድ አያያዝ በመያዝ ያደረሰብን ሁለንተናዊ ተጽፅኖ በምንም የማይተካ ቢሆንም በእስር እና በስቃይ በቆየንባቸው ዓመታት ከደረሰብን ጉዳት እናገግም ዘንድ እኛም እንደ ሌሎች ክልሎች አዲስ አበባን የሚያስተዳድረው አካል ግዴታውን መወጣት ሲገባው ዛሬም እንደትናንናው ክህደት ፈጽመውብናል ፡፡ ስለሆነም እስከዛሬ ከመጣንበት ረጅም፣ አሰልቺና ከባድ ስቃይ ጊዜያትን ስናስብ ካለፍንባቸው መከራ ዘመናት የሚበልጥ አይደለምና ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ በብርቱ መታገላችን ግድ ወደሚልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ፡፡

እኛ በዚህ ማህበር ውስጥ ተሰባበሰብን ያገናኘን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋምና አካባቢያዊነት ወዘተ ሳይሆን የተፈጸመብን ግፍ በመሆኑ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ጥያቄዎቻችን በአፋጣኝ ምላሽ ያገኙ ዘንድ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የሚዲያ አካላት፣ ለዲሞክራሲ መስፈን እና ለሰው ልጆች መብት መከበር የሚታገሉ ድርጅቶችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵ ህዝብ ድምጻችንን እንዲሰማ ከጎናችን እንዲቆምልን አበክረን እንጠይቃለን!

1. ባለፉት አመታት በህገ-ወጡ ህወሓት-ኢህአዴግ መንግስት በግፍ ተይዘን በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ተገደን የሰጠነው ቃል አሻራና የመሳሰሉት ሰነዶች በይፋ ተሰርዘውልን መንግስት ይቅርታ በጠየቀው መሰረት ለተፈጸመብን ግፍ በግልጽና በሰነድ እውቅና እንዲሰጠንና የግፍ ሰነዶቹ መምከናቸውን በይፋ እንዲረጋገጥልን፤

2. እኛ ባለፉት አመታት በግፍ ስንሰቃይ ስንሰደድና በየተዋረዱ ባሉ የመስተዳድር አካላት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረን ሁለንተናዊ መብቶቻችን ሲጣሱ የስራ መብቶቻችን ተገፎ መጠለያ የማግኘት መብት ተከልክሎ፣ አብዛኞቻችን የመኖር መብት ጭምር አጥተንና ከነቤተሰቦቻችን ችግር ላይ የወደቅን በመሆኑ መጠለያ የምናገኝበት መንገድ እንዲመቻችልን፤

3. ባፉት አመታት በግፍ ከፖሊስ ጣቢያ ምርመራ ሂደት ጀምሮ እስከ እድሜ ልክና ሞት ተፈርዶብን ከፍተኛ የአካልና የስነልቦና ጉዳት የተፈጸመብን በመሆኑ እንደየሁኔታው በሀገር ውስጥና በውጭ አገራት በቂ ህክምና እንድናገኝ እንዲደረግልንና ከደረሰብን ጉዳት እንድናገግም ድጋፍ እንዲደረግልን፤

4. ከዚህም በፊት በተደጋጋሚም በጠየቅነው መሰረት ያቋረጥነውን ት/ት እንድንቀጥል የት/ት እድል እንዲመቻችልን፤

5. በጸረ ሽብር ህጉ በግፍ በተያዝንበት ወቅት ከስራችንና ከኑሯችን መፈናቀላችን አንሶብን፤ በላባችን ያፈራነው ንብረቶቻችንን በምርመራ ስም የተዘረፍን እና በየፖሊስ ጣቢያ ተይዘው የቀሩብን በመሆናቸው አንድ በአንድ እንዲመለሱልን፤

6. በሽብር ለተፈረጁ ሁሉ ከውጭ መንግሥታት በኩል የተለገሰው የዕርዳታ ገንዘብ በግልጽና ያለ አድልዎ ለተጎጂዎች፣ ለቤተሰቦቻቸው ወይም ለተወካዮቻቸው በአፋጣኝ እንዲሰጥና ተጎጂዎች በዘላቂነት ሕይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲመቻች፤

7. የሟቾች አጽም ከያለበት በክብር የሚያርፍበት ሁኔታ እንዲመቻችና ለዚህ የሚሆን ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲቋቋም፤ በጀት እንዲመደብ፤ ገዳዮች በህግ እንዲጠየቁ እና የሟች ቤተሰቦች በሁለንተናዊ መልኩ እንዲካሱ፤

8. ለትውልድ ትምህርት እንዲሆን በሕይወት ያሉም ሆነ የሌሉ ታሪካቸው ተጽፎ በብሔራዊ ቤተ መንግስት (አንድነት ፓርክ) ውስጥ መታሰቢያ ሀውልት እንዲሰራላቸው፤

ባጠቃላይ በዳዩን የኢትዮጵያ መንግሥትን የምንጠይቀው ካሳ ወይም ልዩ ጥቅም ሳይሆን የተወሰደብን ጤናችን፣ ክብራችንና ቁሳዊና ሞራላዊ ሀብቶቻችን እንዲመለስልን የምንጠይቅ መሆናችንን ታውቆ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠን፤ ያለበለዚያ መንግስትን በዓለም አቀፍ ህግና በሌሎች ፖለቲካዊ አማራጮች የምንጠይቅ ይሆናል፤

በመጨረሻም እንደ ከዚህ በፊቱ በስቃያችን፣ በመከራችን ወቅት ከጎናችን ለነበራችሁ ኢትዮጵያውያን፣ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ለሰብዓዊ እና ለመብት ተሟጓቾች፣ ለሚዲያ ቤተሰቦች በሙሉ ከልብ የሆነ ምስጋናችንን እያቀረብን አሁንም ትብብራችሁ ድጋፋችሁ እና እገዛችሁ እንዳይለየን በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

የአዲስ አበባ የፖለቲካ እስረኞች አስተባባሪ ኮሚቴ!

ህዳር 25 ቀን 2012

ዋቢ ሸበሌ ሆቴል

አዲስ አበባ


Report Page