#ETH

#ETH


የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ ተቋራጮችን በግብር ስወራ በፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በስምንተኛ እና ዐስረኛ ወንጀል ችሎቶች ክስ መሰረተ።

በኢትዮጵያ ካሉ የደረጃ አንድ ተቋራጮች መካከል እንዲሁም ከፍተኛ አቅም ካላቸው መካከል የሆነው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን፣ ከ 2005 እስከ 2008 ባለው ጊዜ መክፈል የነበረበት እና ከተለያዩ ፕሮጀክቶች የተገኘ 70.3 ሚሊዮን ብር የትርፍ ግብር ባለመክፈሉ ክሱ ተመሥርቷል።

የንግድ ግብሩ ግዢ ባልተፈፀመባቸው ሐሰተኛ ደረሰኞች በመጠቀም የተሰወረ እንደሆነ እና ደረሰኞቹንም የቆረጡት ድርጅቶች በአካል የሌሉ መሆናቸውን ጠቅሶ ነው ዐቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው። ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ከ 25 ሚሊዮን እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገቢን ድርጅቱ ሰውሯልም ሲል ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሰምቷል።

በተጨማሪም ከተለያዩ አገልግሎቶች የተሰበሰበ ሦስት ሚሊዮን ብር የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ በተመሳሳይ ከ 2005 እስከ 2008 ባለው ዓመት ለመንግሥት ሳይከፍሉ ቀርተዋል ሲልም ነው ዐቃቤ ሕግ ክሱን በስምንተኛ የጉምሩክ ችሎት የመሠረተው።

በተመሳሳይ ቻይና ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ከ 2007 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት ካገኘው 375.3 ሚሊዮን ብር ውስጥ 256 ሚሊዮን ብር ባለማሳወቅ የተሳሳተ መረጃ ለገቢዎች ሚኒስቴር በማሳወቅ ክስ ተመሥርቶባቸዋል። በተመሳሳይ በስምተኛ የጉምሩክ ችሎት የተመሠረተው ይኸው ክስ፣ ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የድርጅቱን መረጃ በመደበቅ በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ሲል በተሻሻለው የገቢዎች አዋጅ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሰምቷል።

ድርጅቱ ከተጨማሪ እሴት ታክስ የሰበሰበውን 3.6 ሚሊዮን ብር ላይ አንድ ነጥብ ዘጠኙን በመቀነስ በተመሳሳይ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ገቢ አስቀርተዋል በሚል ተከሷል።

ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ከ2006 እስከ 2008 ድረስ ባለው የግብር ዓመት ከውጪ ምንዛሬ የተገኘ 32 ሚሊዮን ብር ሐሰተኛ መግለጫ በማቅረብ ሰውረዋል ያለው ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ፣ ያለ ደረሰኝ በመገበያየት እና ሽያጫቸውን በመሰወር ወንጀል ፈፅመዋል ሲል በክሱ ላይ አስፍሯል። እንዲሁም በተመሳሳይ የግብር ዓመት ካገኘው 91 ሚሊዮን ብር ውስጥ 45 ሚሊዮን ብሩን በመሰወር ግብሩን አላሳወቀም ተብሏል። ከተጨማሪ እሴት ታክስ የተሰበሰበ ኹለት ሚሊዮን ብር ሳይከፍል ቀርቷል በሚል ነው ክስ የተመሰረተበት። በአጠቃላይም 81.2 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ግብር በመሰወር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክሱን መሥርቷል።

ፓወር ኮን የተሰኘው ሌላው ድርጅት 34 ሚሊዮን ብር ግዢ ሳይፈፅም እንደፈፀመ አድርጎ በማቀረቡ ክስ ልመሠርትበት ችያለሁ ሲል ዐቃቤ ሕግ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክ ችሎት አቤቱታውን አሰምቷል። 59 ሕገ ወጥ ደረሰኞች ከ 12 ድርጅቶች በመጠቀሙ ሆነ ተብሎ በተሰወረ ገቢ መንግሥት ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል በክሱ አስረድቷል።

ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች በፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ተነብቦላቸው ወደ ፍርድ ሂደት እንዲቀርቡ በሚል መጥሪያ የላከ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ጥሪ ተደርጎለት ያልቀረበው ቻይና ፈርስት ሃይዌይ ኮንስትራክሽን ኅዳር 29 በፖሊስ ተይዞ እንዲቀርብ የሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል።

እንዲሁም ቻይና ሬልዌይ ቁጥር ሦስት ኢንጂነሪግ ታኅሳስ አንድ በተላከለት መጥሪያ መሰረት እንዲቀርብ መጥሪያ ፍርድ ቤቱ መስጠቱንም አዲስ ማለዳ ያገኘቸው መረጃ ያስረዳል። ለተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽንም መጥሪያ ከፍርድ ቤቱ የተላከ ሲሆን፣ ለታኅሳስ 13 ተከሳሽ እንዲቀርቡ ታዝዟል።

ከአንድ ዓመት በላይ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ ፌዴራል ፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከ 33 በላይ ደረጃ አንድ ተቋራጮች በተለይም የምርመራ ኦዲት ሪፖርትን መሰረት ያደረገ የምርመራ ሥራ ሲያከናውኑ እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል። ከእነዚህ ተቋራጮች በወቅቱ ከኹለት ቢሊዮን ብር በላይ ተሰውሮብኛል ሲል የነበረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ አብዛኛውን ገንዘብ መሰብሰቡን ቆይቶ አሳውቆም ነበር።

ነገር ግን ፖሊስ የግብር እዳቸውን መክፈላቸው ከፍትኀ ብሔር እዳ እንጂ የወንጀል ምርመራ ከማካሔድ ጋር አይገናኝም በሚል ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር ወራት የፈጀ ምርመራ ሲያካሒዱ ቆይተው፤ ስድስት ድርጅቶች ላይ ክስ መሥርተዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር አዲሱ የበጀት ዓመት ከገባ ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አራት ወራት ውስጥ 90 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን እንዳስታወቀ ይታወሳል።

(Addis Maleda)

Report Page