#ETH

#ETH


ኦነግ ስለ ኦሮሚያ ባለስልጣናት ግድያ ምን ይላል?

በምዕራብ ኦሮሚያ በባለስልጣናት ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ በመንግስት የውስጥ አሻጥር የሚፈጸም ነው ብሎ እንደሚያምን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በተለይ ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ ገለጸ። ኦነግ በግድያዎቹ “እጁ እንደሌለበት፤ የሚያዘውም ሰራዊት እንደሌለው” አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ስላሉ ግድያዎች በጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጥያቄ የቀረበላቸው የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጄላ መርዳሳ “በእኛ ግምት እና በአንዳንድ ምልክቶች፤ የውስጥ አሻጥር የሚመስል ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከመንግስት የውስጥ መዋቅር በተለይም ከመከላከያው እና ጸጥታ ክፍሉ ውስጥ ሆን ብለው አሻጥር (ሳቦታጅ) የሚሰሩ ይኖራሉ” ብለዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በተለይ በአካባቢ ባለስልጣናት እና የስራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ግድያዎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ። በክልሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን ከትናንት በስቲያ በተፈጸመ ጥቃት የጀልዱ ወረዳ ሁለት ባለስልጣናት በጥይት ተመትተው መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

ይህን የምዕራብ ሸዋን ግድያ ጨምሮ ባለፉት ሁለት ወራት በምዕራብ ኦሮሚያ ሶስት ዞኖች ብቻ በትንሹ ስድስት የመንግስት ባለስልጣናት መገደላቸውን ከየአካባቢው የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ግድያዎቹ “በማን እንደሚፈጸሙ በግልጽ የቀረበ ነገር አላየንም” የሚሉት የኦነግ ቃል አቀባይ “የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም ሰዎች ከተማ ውስጥ ይገደላሉ። መንገድ ላይ፣ በመኪናም ሲሄዱ ይገደላሉ” ሲሉ የችግሩን መኖር አረጋግጠዋል።

አቶ ቀጄላም ሆኑ ግድያዎቹ የተፈጸመባቸው አካባቢዎች የመንግስት ኃላፊዎች የገዳዩቹ ማንነት በግልጽ እንደማይታወቅ ቢናገሩም የየአካባቢው ነዋሪዎች ግን ሸኔ ተብሎ የሚጠራው ከኦነግ ተገንጥሎ የወጣ ክንፍ ታጣቂዎች ግድያዎቹን እንደሚፈጽሙ ሲናገሩ ይደመጣል። “ህዝቡ የሚደርሱ ጥፋቶችን ከጠቅላላው የኦነግ አባላት ጋር በማያያዝ ባልተገባ መንገድ ሲያነሳ ይታያል” የሚሉት አቶ ቀጄላ ውንጀላውን ውድቅ አድርገዋል።

“ሸኔ ማለት በድሮው አጠራር የፖሊት ቢሮ አባል ወይም በአሁኑ የመዋቅር ደረጃ የስራ አስፈጻሚ ማለት ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ “በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያለው አደረጃጀት ከድርጅታቸው መዋቅር ውጪ መሆኑን አስረድተዋል። “እኛ የምናዝበት ሰራዊት የለንም። ሰላማዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ነው የመጣነው። አሁንም ፍላጎታችን ያ ነው” ሲሉ ለጀርመን ሬድዮ ተናግረዋል።

(የጀርመን ድምፅ ሬድዮ)

Report Page