#ETH

#ETH


የምዕራብ ኦሮሚያ ባለስልጣናት መገደል!

በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ግድያ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑ ተነገረ። ትናንት በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ ወረዳ ሁለት የወረዳው ባለስልጣናት ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ግድያ አሁንም ቀጥሏል። በምዕራብ ሸዋ ዞን የጀልዱ ወረዳ ሁለት ባለስልጣናት ትናንት ማክሰኞ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል። ትናንት ከተገደሉት ከሁለቱ የጀልዱ ወረዳ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ገዳዮቹ አለመታወቃቸውን እና ፖሊስ የማጣራት ስራ እየሰራ መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገላና ኑረሳ ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ ተናግረዋል።

በትናንትናው የጎጆ ከተማ ግድያ ሕይወታቸውን ያጡት የጀልዱ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ረጋኔ ከበደ እና በወረዳው የኦዲፒ ጽ/ቤት የከተማ ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ገረመው መሆናቸውን የወረዳዋ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የኮሙኒኬሽን ባለሞያ አቶ ቢቂላ አበበ ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ ገልጸዋል።

ባለስልጣናቱ የተገደሉት ትናንት አመሻሽ አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ከመስሪያ ቤታቸው ወጥተው ወደ ቤት እየሄዱ ባሉበት ወቅት ባልታወቁ ሰዎች በጥይት ተመተው መሆኑንም አቶ ቢቂላ አስረድተዋል።

ከሁለቱ የጀልዱ ወረዳ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 11 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ቢቂላ ገልጸዋል። ሕገ ወጥ የቤት ግንባታን ከማፍረስ ጋር በተያያዘ ጥቅማቸው የተነካባቸው ያሏቸው ሰዎች ግድያውን በተደራጀ መንገድ ሳይፈጽሙ እንዳልቀረ ጥርጣሬ እንዳላቸው አቶ ቢቂላ ተናግረዋል። ነገር ግን ፖሊስ የምርመራ ስራውን አከናውኖ ሲጨርስ ጉዳዩ ተጣርቶ እንደሚታወቅ የኮሚኒኬሽን ባለሞያው አብራርተዋል።

የወረዳዋ ባለስልጣናት ግድያ እንደተባለው ከአስተዳደራዊ ችግር ጋር በተያያዘ አልያም ከጀርባው ሌላ ምክንያት ስለመኖሩ ከሌላ ገለልተኛ አካል ለማጣራት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። በሌላ በኩል የሁለቱ ባለስልጣናት አስክሬን ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ መላኩንም ለጀርመን ድምፅ ሬድዮ አረጋግጧል።


በምዕራብ ኦሮሚያ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረው ግድያ በሳምንት ውስጥ የትናንትናዉ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። የዛሬ ሳምንት ኅዳር 10/2012 በምዕራብ ወለጋ ዞን ላሎ አሳቢ ወረዳ ውስጥ የኦሮሚያ የመንገዶች ባለስልጣን የኮሚኒኬሽን ኃላፊ የነበሩት አቶ ቶላ ገዳ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። የትናንቱን የምዕራብ ሸዋውን ግድያ ጨምሮ ባለፉት ሁለት ወራት በምዕራብ ኦሮሚያ ሦስት ዞኖች ብቻ በትንሹ 6 የመንግስት ባለስልጣናት መገደላቸውን ግድያዎቹ ከተፈጸመባቸው አካባቢዎች የመንግስት ሃላፊዎች አስታውቀው ነበር።

(የጀርመን ድምፅ ሬድዮ)

Report Page