#ETH

#ETH


የሦስት ሰዎችን ሕይወት በተመሳሳይ አጥፍተዋል የተባሉት ግለሰብ አንድ ሰው ላይ ሙከራ አድርገዋል

በአዲስ አበባ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ኸለት ልዩ ሥሙ አሜን ሆስፒታል ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ሚሊዮን ዘሪሁን የተባለ የጎዳና ተዳዳሪ በሌላ ጎዳና ተዳዳሪ ላይ በበቀል ስሜት በመነሳሳት በፈፀመው የግድያ ወንጀል ተፈረደበት።

ሟች በራሱ ላይ በተጫነበት ከፍተኛ መጠን ያለውን ድንጋይ፣ የራስ ቅል አጥንት መሰባበር እና የአንጎል ወደ ውጪ መውጣት ደርሶበት ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ ተከሳሽ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሏል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ሲመለከት በቆየው መዝገብ ላይ እንደተረጋገጠው፣ ተከሳሽ ሟች እና ጓደኞቹ ጋር ‹‹የጉልበት ሥራ በመሥራት የተገኘውን ገንዘብ ሳይከፍሉኝ ቀርተዋል፤ በጋራም በመሆን ድብደባ ፈጽሞብኛል›› በሚል ምክንያት በቂም በመነሳት ወንጀሉን ፈፅሟል። በዚህ ምክንያትም ሟች የሚያድርበትን አካባቢ ሲያጠና ከቆየ በኋላ በግምት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ሲሆን ሟች በጎዳና ላይ የግንብ አጥር ስር ተኝቶ ባለበት ቦታ በጭካኔ ሕይወቱ እንዲልፍ አድርጓል በሚል ተከሷል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ የ28 ዓመት ወጣት የሆኑት ተከሳሽ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 ተላልፈዋል የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ በዚህ መሰረትም አምስት ክሶችን አቅርቦባቸዋል። ዐቃቤ ሕግም ግንቦት 17/2010 ማንነቱ ባልታወቀው ግለሰብ ላይ የተፈጸመውን ወንጀል ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰው፤ የሰነድ እና ገላጭ ማስረጃዎች በመያዝ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም ተከሳሽ በተመሳሳይ ቦታዎች በጎዳና የሚኖሩ እና ማንነታቸው ያልታወቀ በሚል በአስክሬን ቁጥር ብቻ በተለዩ ግለሰቦች ላይ በተለያዩ ቀናቶች ሦስት ከባድ የግድያ ወንጀል ፈፅመዋል ሲል ከኹለተኛ እስከ አራተኛ ክስ ያቀረበው አቤቱታ ዝርዝር ያስረዳል።

ዐቃቤ ሕግ በአምስተኛ ክሱ ላይ እንዳስረዳው አንድ ሕይወታቸው በህክምና መትረፍ የቻሉ ሌላ የጎዳና ተዳዳሪ ላይ ‹‹የምተኛበትን ካርቶን ወሰድክብኝ›› በሚል ምክንያት በተፈጠረ ጸብ ተበዳይ ተኝተው ባሉበት ድንጋይ በማንሳት ጭንቅላታቸው ላይ እንዲሁም ከተኙበት ቀና ሲሉ ድንጋይ በመወርወር ግንባራቸው ላይ በመምታት ከፍተኛ ጉዳት በግድያ ሙከራ ወንጀል በሚል ተከሷል።

የሰው፣ የሰነድ እና አካባቢያዊ ማስረጃዎችን ሲሰማ የቆየው ችሎቱ፣ ተከሳሽ ጥፋተኛ የተባለበት አንደኛ ክስ በዕድሜ ልክ እስራት ወይም ሞት የሚያስቀጣ በመሆኑ አንዱ ክስ ብቻ እንዲያዝ በማድረግ መነሻ የዕድሜ ልክ እስራት እንደሚያስቀጣ ጠቅሷል።

ነገር ግን ተከሳሽ ከዚህ ቀደም የወንጀል ጥፋትን በተመለከተ በፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ያልተባለ መሆኑ ከተያዙለት አራት የቅጣት ማቅለያዎች መካከል ሆኗል። በተጨማሪም ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በለመሆኑ እና በትምህርት ያልበሰለ መሆኑ ክሱን ለማቅለል ፍርድ ቤቱ የተቀበላቸው ምክንያቶች ነበሩ።

በዚህ መሰረትም ኅዳር 3/2012 በዋለው ችሎት ተከሳሽ የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈርዶበታል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሥነ -ልቦና ባለሞያ ሰናይት ተመስገን፣ እንዲህ አይነት የፍርድ ሒደቶች የጥፋተኛውን የአዕምሮ ጤንነት ማየት እና የጥፋተኝነቱን የኋላ ዳራ መመልከት ያስፈልጋቸዋል ይላሉ።

‹‹የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት ግን እንደ ማኅበረሰብ አሳሳቢ ቢሆንም ለአካላዊ ጤንነት እና ደኅንነት እንደምንጨነቀው ሁሉ የአዕምሮ ጤና ላይ ያለን ትኩረት ሊዳብር እንደሚገባው ያሳያል›› ብለዋል። ‹‹በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የአዕምሮ ጤንነት መጠበቅ እና ትኩረት መስጠት እንደሚገባን የሚያሳይ ድርጊትም ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ሙያዊ አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ነገር ግን የአዕምሮ ጤንነት ለጥፋቶች ምክንያት አድርጎ ማቅረብን ሳይሆን የጉዳት መጠንን መቀነስ የሚታሰብበት፤ ፍርደኞች ከእርምት ሲወጡ ጭምር ጥፋታቸውን እንዳይደግሙት በሚደረግላቸው ክትትል ጭምር መሆን እንዳለበትም ባለሞያዋ አጽንኦት ሰጥተውታል።

(አዲስ ማለዳ)

Report Page