#ETH

#ETH


ውህደቱ ከፌዴራል ሥርዓቱ እና ከህገመንግስቱ ጋር ፍፁም ተቃርኖ የሌለው መሆኑ ተገለጸ!

አቶ ካሳሁን ጎፌ፦

• ህዝብን ጠላትና ወዳጅ ብሎ የመከፋፈል ሁኔታን የሚያስቀር፣

• ኢትዮጵያዊ ማንነትንና የብሔር ማንነትን አጣጥሞ ለመምራት የሚያስችል ነው

ኢህአዴግ ከፌዴራል ሥርዓቱ እና ከህገመንግስቱ ጋር በፍፁም ተቃርኖ በሌለው መልኩ ራሱን ያሻሻለ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) አስቸኳይ ጉባኤ በመጥራት ለሁለት ቀን በአዳማ ሲመክር ቆይቶ የውህደቱን አጀንዳ አፀደቀ፡፡

በፓርቲው ፅህፈት ቤት ለጋዜጠኞች በተሠጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኦዲፒ ማዕከላዊ ፅህፈት ቤት የከተማ አደረጃጀትና የፖለቲካ ዘርፍ አላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ፤ ፓርቲው እሻገርበታለሁ ባለው ሂደት ከፌዴራል ሥርዓቱ እና ከህገመንግስቱ ጋር በፍፁም ተቃርኖ በሌለው መልኩ ራሱን እያሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፓርቲ ሪፎርሙ ዘመኑን የሚመጥን አደረጃጀት ይዞ የመቀጠል ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም፤ ለሁሉም ህዝቦች የተመቸቸ ሁኔታን ለመፍጠር፤ ህዝብ ጠላትና ወዳጅ ብሎ የመከፋፈል ሁኔታን ለማስቀረትና የጎራ አሰላለፍና የሃይል ፍረጃ ቀርቶ ሰዎች የማይሸማቀቁባትን እንዲሁም በነፃነት ሃሳባቸውን የሚገልፁበትን ሁኔታ ለመፍጠር የፓርቲ ሪፎርሙ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበ ወደ ውህደት መመጣቱን ተናግረዋል፡፡

አቶ ካሳሁን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አፅድቆ ለኢህአዴግ ምክር ቤት የላከው ውህደት፤ ከህውሐት በስተቀር ሁሉም አባልና አጋር ፓርቲዎችን ጨምሮ በሙሉ ድምፅ የውህደቱን አጀንዳ መፅደቁን አስታውሰው፤ ነገር ግን በኦዲፒ ህገ ደንብ መሰረት የመጨረሻውን ውህደት አጀንዳ ማፅደቅ ያለበት ጉባኤው በመሆኑ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከሁለት ሶስተኛ በላይ አባላት እና ከአንድ ሶስተኛ በላይ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አባላት ሃሳቡን ወስደው ለሁለት ቀን የመከሩበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው የአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራም በዝርዝር ቀርቦ የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እየመሩት በቡድን ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱም ላይ የሁሉም ህዝብ ጥያቄ ምላሽ ሲያገኝ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄም ምላሽ ያገኛል በሚል ጉባዔው መተማመን መቻሉንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነትንና የብሔር ማንነትን አጣጥሞ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን አስመልክቶ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በተነሱ ጉዳዮችና ባልተቋጩ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶ የውህደት አጀንዳውን ጉባኤተኛው በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል ብለዋል፡፡

ኦዲፒ በራሱ ህገ ደንብ አንቀጽ 16 ተራ ቁጥር 3 መሰረት አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቶ ውህደቱን ማፅደቁም ተጠቁሟል፡፡

(ኢፕድ)

Report Page