#ETH

#ETH


የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃን ለመከላከል በወጣው ረቂቅ አዋጅ የተደነገገው ቅጣት አነስተኛ ነው ሲሉ የሕዝብ እንደራሴዎች አባላት ተችተውታል፡፡

የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ የሚደነግገው ከፍተኛ ቅጣት የ5 ዓመት ፅኑ እስራት ነው፡፡ ይህም አስተማሪ አይሆንም ተብሎ ተተችቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት በግለሰብ ወይንም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈፀመ ወይም የተሞከረ እንደሆነ ድርጊቱን የፈፀመው ሰው እስከ 5 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ በአንቀፅ 5 ደንግጓል፡፡

5 000 ተከታይ ባለው የማህበራዊ ድረገፅ ላይ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያነሳሳ የጥላቻ መረጃ መለጠፍም ሆነ በብሮድካስት አገልግሎት እና በህትመት ውጤቶች ላይ ፅፎ የተገኘም እንደሆነ እስከ 3 አመት የሚደርስ ቀላል እስራት ወይንም 100 000 ብር ቅጣትን ይደነግጋል፡፡ ቀላል እስራት ከተባለ የሚጀምረው ከ10 ቀን ነው ያሉት የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት፣ የተደነገገው ቅጣት አስተማሪ አይደለም የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሌላ በኩል የዜና ዘገባ፣ የፖለቲካ ትችት፣ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶች፣ የጥላቻ ንግግሮችን ለመቆጣጠር የወጣው ረቂቅ አዋጅ አይከለክላቸውም መባሉ ትክክል አይደለም ሲሉ እንደራሴዎቹ ሞግተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዜና በሚመስልና በሌላም መንገድ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር የጥላቻ ንግግር፣ የሌላውን ክብር የሚያጎድፍና ለግጭት የሚያነሳሳ ሀሳብ እየተሰራጨ ነው ያሉት እንደራሴዎቹ፣ የዜና ዘገባ፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ የኪነ ጥበብ ስራዎች እንዲሁም የፖለቲካ ትችቶችን ጭምር ረቂቅ አዋጁ አይመለከታቸውም መባሉን ተቃውመዋል፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በህገ መንግስቱ የተፈቀደ ነውና በጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ማፈን ከተጀመረ ወደ ኋላ ይመልሰናል የሚል ስጋታቸውን አንድ እንደራሴ ገልፀዋል፡፡ የተነሱ አስተያየቶችን ሁሉ አካትቶ በዝርዝር ፈትሾ ማስተካከያ የሚያሻቸውን አንቀፆችን እንዲያስተካክል ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁ ተመርቷል።

(SHEGER FM)

Report Page