#ETH

#ETH


የተባበሩት መንግስታት / UN-HABITAT/ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በከተማ አጀንዳ ዙሪያ የጋራ ምክክር አካሄዱ

በኢትዮጵያ መንግስት ግብዣ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የተባበሩት መንግስታት   / UN-HABITAT/ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ማሂሙናህ ሞሃድ እና ከእርሳቸው ጋር የመጡት ሌሎች የልዑካን ቡድን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር በከተማ አጀንዳ ዙሪያ የጋራ ምክክር አደረጉ፡፡ 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ በከተሞች የተሻሉ ስራዎች ለመስራትና ከተሞችን ይበልጥ ለነዋሪዎቻቸው ፅዱ፣ ውብ፣ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ያዘጋጀውን የ10 ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ አቅርቧል፡፡ በቀረበው ዕቅድ ላይም በአሁኑ ሰዓት በከተሞች የሚታየውን የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር፣ የቤት ልማት እጥረት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት፣ የቴክኖሎጂ እና የፋይናንስ እጥረት ችግሮች በዋናነት የተነሱ ሲሆን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተባበሩት መንግስታት /UN-HABITAT/ ጋር በጋራ ለመስራትና ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችለውን አሰራርና አደረጃጀት በእቅዱ አመላክቷል፡፡ 

የተባበሩት መንግስታት / UN-HABITAT/ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ማሂሙናህም እቅዱ ጥሩና አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም በከተሞች የተሻለ ስራ በጋራ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመሆን ዘርፈ-ብዙ ስራዎች እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል፡፡ 

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ክብርት ኢንጅነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው አሁን ያለንበት ዘመን የብልፅግና ዘመን እንደመሆኑ መጠን ከተሞቻችንን የብልፅግና ማዕከላት ለማድረግ ከሚመለከታቸው ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ ክብርት ሚኒስትሯ አያይዘውም በተለይ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት በከተሞቻችን በስፋት የሚታዩ የስራ አጥነት፣ የቤት እጥረት እና በከተሞች ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ ከ UN-HABITAT ጋር በቅርበት አየሰራን የምንገኝ ሲሆን ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል ሃገር እንደመሆኗ መጠን ድርጅቱ ከተሞችን ለመምራትና ለመቆጣጣር በምናደርገው ስራ በተለያዩ ዘርፎች የተሻለ ድጋፍና ክትትል እያደረገልን ይገኛል ብለዋል፡፡

(Negede Moges)

Report Page