#ETH

#ETH



 የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለሲዳማ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ የሲዳማ ህዝብ ህዳር 10 2012 ዓ.ም ባካሄደው ህዝበ ውሳኔ ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመልእክታቸውም፥ “ከሁሉም በፊት ህገ መንግስታዊ መብታችሁን ተጠቅማችሁ ለዚህ ድል በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል።

ከ20 ዓመታት ትግል በኋላ በአንድ ዓመት ተኩል የለውጥ ጉዞ ምእራፍ ውስጥ የሲዳማ ህዝብ ያገኘው ድል የህዝብ የነፃነትና ሉአላዊነት ምልክት ሆኖ በታሪክ መዝገብ በመስፈር ሌላኛው የስኬት አቅጣጫ ነው ብለዋል።

ሲዳማ ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ ለረጅም ዓመታት መልስ ያሳገኝ ቆይቷል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ይሁን እንጂ ህዝብን የማዳመጥ ውጤት የሆነው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተደርጎ ሲዳማ 10ኛው የፌዴሬሽኑ ክልል መሆኑ እውነተኛ ህብረ ብሄራዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ስራ ላይ መዋል መጀመሩን ያመላክታል ሲሉም ገልፀዋል።

ከሁሉም በላይ የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ያሳየው ስነ ምግባር በጣም የሚያኮራ እና የሲዳማ ህዝብ ያለውን የሰላም እሴት ያሳየ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፥ ሰላምና መረጋጋት ባለበት ድል እንዳለም ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

በመጨረሻም ከሲዳማ ህዝብ እና ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በመሆን ህብረ ብሄራዊ የፌደራል ስርዓት ለመገንባት የክልሉ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነትም አረጋግጠዋል።

በተያያዘ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ለሲዳማ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፏል።

የትግራል ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫው፥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ማረጋገጥ፣ በማንም የማይገረሰስ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ሉአላዊነት መግለጫ ነው ብሏል።

የሲዳማ ብሄር የራሱን ክልላዊ መስተዳደር አቋቁሞ ለመተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የሚከበርበት ዋዜማ ላይ ሰላማዊና ህጋዊ ስርኣቱ በተከተለ አገባብ በህዝበ ውሳኔ በማረራጋገጡ በትግራይ ህዝብ እና በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስም እንኳን ደስ አላቹሁ ብሏል ቢሮው በመግለጫው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ለሲዳማ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ባሰሩት ጽሁፍ፥ “ለሲዳማ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንኳን ደስ አላችሁ፤ ይህ ድላችሁ ነው” ብለዋል።

(FBC)

Report Page