#ETH

#ETH


የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም

ሃዋሳ

የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ህዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ህዝብ ውሳኔ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ተካሂዷል።

የህዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ህዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ እለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ቦርዱ የህዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈፀም ሀላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞን እና በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድሎ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት አሰራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ህዝብ ውሳኔ አፈፃፀም መመሪያ በማጽደቅ ነው፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የህዝብ ወሳኔውን የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉ እና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስ ለህዝብም ይፋ እንዲሆን ተደርጓል። ቦርዱ በህዝብ ውሳኔው እቅድ አፈፃፀም ከክልሉና የዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይት እና ስምምነቶችን አድርጓል። በዚህም መሰረት ለህዝብ ውሳኔ ማስፈፀሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግስት እንዲፈቀድ ተደርጓል። ህዝብ ውሳኔው በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈፀም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሰረት የህዝቡ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚል ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃንና አዲስ በሚፈጠረው እና ነባሩ ክልል መሃከል የሚኖረውን የሃብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና በህግ ማእቀፍ አውጥቶ አቅርቧል፡፡

በቅድመ ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት በቦርዱ ባለሞያዎች የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል፡፡። በዚህም መሰረት ለህዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የህዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ ከዞኑ፣ ከሃዋሳ ከተማ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና አስተዳደር ተቋማት የህዝበ ውሳኔው ፀጥታ እቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡ የእቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ከቅድመ ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድህረ ህዝበ ውሳኔ የነበረው የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ በዚህ እቅድ መሰረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።

ህዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በህግ መሰረት የሚያስፈፅሙ 6843 አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮምያ ክልል አከባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች ህዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስልጠናውም ቀድመው የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ 20 አሰልጣኞች ለ5 ቀናት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ ማንዋል እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

የመራጮች ምዝገባ በዞኑ እና በሃዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛውም ህጋዊ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 06/2012 ዓ.ም ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበዋል፡፡

የድምጽ ሰጪዎች ህዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምጽ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልእክቶች ተላልፈዋል፡፡ በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብ እና የሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው የቦርዱ አመራር አባላት በሃዋሳ፣ በይርጋአለም፣በወንዶ ገነት፣ በበሌላ፣ በመዘዋወር የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶች እና የአሰራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እንዲሁም በድምጽ መስጠት ሂደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጓል፡፡ በደረሱት ጥቆማዎችም መሰረት የተለያዩ ማስተካከያ እርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶች እና ቀደም ብሎ ከዞኑ እና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በህዝበ ውሳኔው ሂደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ

- የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ጸጥታ አጠባበቅ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡

- በህዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፤

- በህዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባ እና ድምጽ መስጠት ሂደት ሁለቱም አማራጮችን የሚወክሉ ወኪሎች አንዲገኙ ጥረት ተደርጓል፡፡

- የተጓደሉ የህዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ ተደርጓል፡፡

የህዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሰራሮች ትምህርት ለመውሰድ ለ128 የሲቪል ማህበራት ታዛቢዎች እና 74 የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሂደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል እውቅና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ህዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ተደርጓል፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት ህዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካን መንግስት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ህዝበ ውሳኔን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል፡፡

የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ ሲሆን በዚህም ሂደት 3000 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች እና 2.5 ሚልዮን በላይ ( መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኗል፡፡

በህዝበ ውሳኔው ሂደት ጸጥታ እና ደህንነት አስመልክቶ ቦርዱ ሂደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሃዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት አድርጓል፡፡ ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ እና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማህበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል፡፡ ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል የጸጥታ አካላት፣ የፌደራል ፓሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ኅዳር 10 ቀን የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ በእለቱ የቦርድ አመራር አባላት የመስክ ጉብኝቶችን ያካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቆጠራውም በእለቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተለጥፏል፡፡ በእለቱ ከመራጮች የሚመጡ ጥቆማዎችንም መሰረት በማድረግ የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ሲከናወኑ ውለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በአጠቃላይ ከተመዘገበው 2,280,147 መራጭ 2,277,063 ሰው ድምጹን ሰጥቷል፡፡ ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ ( voter turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጠ ሰው ብዛት 33,463 ሲሆን የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጠ ሰው ብዛት 2,225,249 ነው፡፡ በውጤቱም ሻፌታ የመረጠው 98.51 % ሲሆን ጎጆን የመረጠው 1.48 % ነው፡፡ ፡፡ በሂደቱ የዋጋ አልባ ድምጽ ቁጥር 18,351(0.000002%) ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገመንግስት አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የራሱ ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሰረት የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡ የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሣኔ መሰረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል፡፡

የህዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው፡፡ ህዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ ያምናል፡፡ በውጤቱ መሰረትም በህገ መንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የህዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ህዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና እምነት አለው፡፡

ያጋጠሙ ተግዳሮቶች

የህዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ሰላማዊና ህጋዊ መሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ በጎ ውጤት ሲሆን፣ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንጻር የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነው ብሎ ያምናል፡፡ የአፈፃፀም ሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ ለቀጣይ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤

•የህግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፤ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት

•የህዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሂደት የአንድን ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑ እና የህዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግስት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ

•የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የህዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር

•በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማን የገጠር አካባቢ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅእኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት

•በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ

•በህዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሃዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድ ተቋማት ሃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመመገመት (Projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ

•በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በህግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻ እና መዝጊያ ሰአት አለመጠበቅ እንደዋና ተግዳሮት የሚጠቀሱ ሲሆን ማለትም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የደቡብ እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት) የህዝበ ውሳኔ ቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የአካባቢ ጸጥታ እና ደህንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ስምሪትን እንዲሁም ድምጽ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሰገን ድጋፍ ማድረጋቸው እና በህዝበ ውሳኔው ሂደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው፡፡

ምስጋና

በሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ እስካሁን በሃገራችን ከነበረው ልምድ የተለየ እና መጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም ችሏል፡፡ ይህንን ህዝበ ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ቦርዱ ከተለያዩ አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት የኢትዪጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚከተሉት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

-በህዝበ ውሳኔው በሰላማዊ እና ስነሰርአት ባለው ሁኔታ ለተሳተፉት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሙሉ

-ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ባልተሟላ አንዳንዴም በአስቸጋሪ ሁኔታ ህዝበ ውሳኔውን ላስፈጻሙ የህዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች እና ስራውን በማስተባበር ለደከሙ የቦርዱ ሰራተኞች

-ለህዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች ምልመላ ድጋፍ ያደረጉልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ፣ ለአ.አ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ፣ የአአ ትምህርት ቢሮ፣ የአአ ጤና ቢሮ

-ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤትለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ርእሰ መስዳድር እና የርእሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት

-ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት

-ለሲዳማ ዞን አስተዳደር

-ለሃዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት

-ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሃገር መከላከያ ሰራዊትና ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደቡብ እዝ

-ለፌደራል ፓሊስ

-ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፓሊስ ኮሚሽን

-ለሲዳማ ዞን ፓሊስ

-ለሃዋሳ ከተማ ፓሊስ

-ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

-ህዝበውሳኔውን ለመታዘብ ለተሳተፉ ሲቪል ማህበራት

-የተለያዩ እገዛን ላደረጉልን የአሜሪካን የልማት ድርጅት (USAID/IFES) እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት (UNDP)

-ለአዲስ ፓርክ

Report Page