#eth

#eth


ከነገ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በማይገቡ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል!

ከነገ ጀምሮ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት ካልገቡ መንግስት ቀጣዩን እርምጃ እንደሚወስድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳይንስና ከፍተኛ የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ችግር ተከስቶባቸው ከነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል በተወሰኑት መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል።

በዚህም ወልዲያ፣ ወለጋ፣ አምቦ እና አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ቱሉ ዲምቱ) ዩኒቨርሲቲዎች አሁን ላይ መረጋጋት የተስተዋለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።

ከነገ ጀምሮም መንግስት የፀጥታ መሻሻል ባልታየባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ቀጣዩን እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት።

በተለይም መቱ እና ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲዎች ከነገ ጀምሮ ወደ ስራ ካልገቡ ቀጣይ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲስተጓጎል ተማሪን ከተማሪ በማጋጨት፣ ምግብ በመከልከል፣ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ በማድረግና በሌሎች መሰል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ተማሪዎችና ተማሪ ያልሆኑ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም አንስተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ወደ 100 የሚደርሱ ተማሪዎች እንዲሁም ተማሪ ሳይሆኑ የዩኒቨርሲቲ መታወቂያ፣ የተለያዩ ሰነዶች፣ በርካታ የባንክ ሂሳብ ደብተሮችና ሌሎች መረጃዎችን የያዙ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይም ማጣራት ተደርጎ በየተቋማቱ አስተዳደራዊና በወንጀል ተጠያቂ እንደሚደረጉም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በዚህ ድርጊት ተሳትፎ ነበራቸው ብለዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በሚገኙበት አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የሃገር ሽማግሌዎች የመማር ማስተማሩ ሂደት ወደነበረበት እንዲመለስ ለሰሩት የማረጋጋት ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

(FBC)

Report Page