ETH

ETH

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

ከመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት የተሰጠ መግለጫ!

በመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስቆም እና የቀጠናውን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ ከወራት በፊት ጀምሮ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በርካታ ስራዎች ሲሰራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል።

በዚህም መሠረት፦ 

1. ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ከሕወሓት የጥፋት ተልዕኮ በመውሰድ የአከባቢውን ሠላም ሲያናጉ የነበሩ በርካታ የፀረ-ሠላም ኃይሎችን መደምሰስ፣ መማረክ እና በርካቶች ደግሞ ለህግ እንዲቀርቡ አድርጓል።

2. ከዚህ በተጨማሪም በዞኑ በሁሉም አከባቢዎች የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር  የመከላከያ ሠራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልሉ ፀረ-ሽምቅ አባላት፣  የአከባቢው ሚሊሻዎች እና የግል ታጣቂዎች በተቀናጀ መልኩ የህብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት በማስጠበቅ ረገድ መጠነ-ሰፊ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ በተሰራው ስራም ውጤቶች ተገኝተዋል።

3. የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ወደፊትም ቢሆን የአከባቢውን ሠላም በሚያውኩ ፀረ-ሠላም ኃይሎች ላይ የተጀመረውን የተቀናጀ እርምጃ የበለጠ በማጠናከር፣ አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ህረተሰቡ በሚገባ ሊገነዘበው ይገባል።

4. ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለፈው ሳምንት በድባጤ ወረዳ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ባደረሱ ፀረ-ሠላም ኃይሎች የጸጥታ አካላት በወሰዱት ቁርጠኛ እርምጃ ከ20 በላይ የሚሆኑ ፀረ-ሠላም ኃይሎችን መደምሰስ ተችሏል።

4. ሠራዊቱ በድባጤ ወረዳ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ለማረጋጋት እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት፣  ከዚህ በፊት በአከባቢው አንጻራዊ  ሠላም  የሚታይበት እና ምንም እንኳን በኮማንድ ፓስት ስር የሚተዳደር ቢሆንም መነሻውን ቡለን ወረዳ  ዶቢ  ቀበሌ ያደረገ የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪ  በመንቀሳቀስ ላይ እያለ በድባጤ ወረዳ ቂዶህ ቀበሌ ሲደርስ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ደርሷል፡፡  በንጹኃን ዜጎች ላይ በደረሰው ጉዳትም የዞኑ ኮማንድ ፖስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ 

ጸረ-ሠላም ኃይሎች በተሳፋሪዎች ላይ ያደረሱት ጥቃትም አንድን  ብሄር  ብቻ  ዓላማ ያደረገ ሳይሆን በተሽከርካሪ ውስጥ ባሉት ሁሉም ዜጎች ላይ የደረሰ ጥቃት መሆኑን ህብረተሰቡ  ሊገነዘብ ይገባዋል። በአካባቢው የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠርም ኮማንድ ፖስቱ በትኩረት እየሠራ ይገኛል፡፡

5.  ኮማንድ ፖስቱ በንጹኃን ዜጎች ጥቃት አድራሾች ላይ የጀመረውን እርምጃ እና የህግ የበላይነት የማስከበር  ተግባር  ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር ተልዕኮውን በቁርጠኝነት እንደሚወጣ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ ይወዳል።

ይሁን እንጂ ኮማንድ ፖስቱ ከታወጀ ጊዜ አንስቶ በዞኑ የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር  ለመፍታት የዜጎችን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በአንዳንድ ጽንፈኛ ተልዕኮ ባነገቡ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በኩል በተደጋጋሚ ከላይ የተከናወኑትን ተግባራትና የተገኙ ውጤቶችን በተጨባጭ እና ነባራዊ ሀቁ  ባላገናዘበ መልኩ ኮማንድ ፖስቱ የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ እንዳልሆነ በማንሳት የሚያራግቡ ቡድኖች እና ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኮማንድ ፖስቱ በጥብቅ ያሳስባል።

መጨረሻም ከህወሓት የጥፋት ተልዕኮ የተሰጣቸው የጸረ- ሠላም ኃይሎች እዚህም እዚያም በሚፈጥሩት የፀጥታ ችግር ህብረተሰቡ ሳይረበሽ እንደ ከዚህ በፊቱ ከቀበሌ ሚሊሻዎች ጀምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጎን በመሆን በተጀራጀ መልኩ  የአከባቢያቸው ሠላም  እንዲጠብቁ  ኮማንድ ፖስቱ ጥሪውን ያቀርባል።

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት

ህዳር 09/2013 ዓ.ም፣

Report Page