#ETH

#ETH


“ዩኒቨርሲቲ የመማሪያና የምርምር እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ ቦታ አይደለም” - ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፡- ዩኒቨርሲቲዎች የመማሪያና የምርምር ቦታ እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ ቦታ አለመሆናቸውን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቦች መገንዘብ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲዎች የመማሪያና የምርምር ቦታ እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ ቦታ ባለመሆናቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎችና የዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቦች ተገንዝበው የሚነሱትን ችግሮች መመከት ይኖርባቸዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህንን በማክበራቸው ሠላማዊው የመማር ማስተማር ሂደት ቀጥሏል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በሌላ ቦታ የሚታየው ችግር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አላጋጠመም። የተቋሙ ተማሪዎች በፈለጉት ጉዳይ ዙሪያ ሀሳብ እንዲለዋወጡ፣ እንዲወያዩ እንዲከራከሩና በሀሳብ ልዕልና እንዲያምኑ እድል ስለሚሰጣቸው እኩይ ለሆኑ ተግባራት አይጋለጡም። ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በተቋሙ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ክበባት የመዝናኛ መርሐ ግብሮች እንዲዘጋጅላቸው ይደረጋል። በዚህም እርስ በርሳቸው በመከባበር ሠላማዊ ቆይታ እያደረጉ ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመንግስትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ስለሚሰራ ሌሎች ቦታዎች የተስተዋሉ ችግሮች እንዳልገጠሙት የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በሌሎች ቦታዎች የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተማሪዎችን ማዕከል አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ በመጠቆም፤ ተማሪዎችም ሆኑ የዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰቦች ይህንን መመከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። “ዩኒቨርሲቲ የመማሪያና የምርምር ቦታ እንጂ የፖለቲካ ማራመጃ አይደለም። ፖለቲካዊ ሀሳቦች አይነሱ ማለት አይደለም።

እንደተመራማሪ በሀሳብ የመሟገት መርኅን መከተል አለባቸው። ተቋማት ከመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት መስራት አለባቸው። የየተቋማቱ ቅጥር ግቢ ዙሪያም ለማማር ማስተማር ምቹ ካልሆኑ ንግድ ቤቶች ጽዱ መሆን አለበት። የአስተዳደርና የጸጥታ አካላትም የፖለቲካ ሥራ የሚሰሩበት ሳይሆን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲኖር አጋዥ መሆን አለባቸው” ሲሉም አስገንዝበዋል።

Report Page