#ETH

#ETH


በዩኒቨርስቲዎች አሁናዊ የፀጥታ ሁኔታዎች ላይ የቀረበ መረጃ፦

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርስቲዎች አሁናዊ ጉዳዮች ላይ የሚነሱ ሃሰተኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን ለማጥራት ይቻል ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ በቀን ሁለት ጊዜ ዩኒቨርስቲዎቹ ያሉበትን ዕለታዊ መረጃ ያቀርባል፡፡ ይሄንንም ዘገባ በሚከተሉት አድራሻዎች ማግኘት የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

http://moshe.gov.et/

https://twitter.com/she_ethiopia

Ministry of Science and Higher Education - Ethiopia

የዛሬው የዩኒቨርስቲዎች ውሎ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርስቲዎች ያሉበትን የፀጥታ ሁኔታ በመከታተል የሚስተዋሉ ችግሮችን ከተቋማቱ ጋር በመሆን ለመፍታት ይሰራል፡፡ በየቀኑም የመረጃ ልውውጥ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት ህዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም ሁሉም ዩኒቨርስቲዎቻችን ያሉበት ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡

• ትናንት ማምሻውን ወሎና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች በተወሰኑ ተማሪዎች መካከል ድንጋይ የመወራወር ሙከራ ነበር፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ምንም አይነት የከፋ ጉዳት አልደረሰም፡፡

• ዛሬ ማለዳ ወልዲያና ኦዳቡልቱም ዩኒቨርስቲዎች በቁርስ ሰዓት በተወሰኑ ተማሪዎች መካከል ግጭት የመፈለግ አዝማሚያ ተስተውሏል፡፡ እንደምክንያት የሚያነሱት ደግሞ በሌላ ዩኒቨርስቲ ያሉትና ምግብ ያቆሙት ተማሪዎች እስካልተመገቡ ድረስ አንመገብም በሚል ነበር፡፡

• ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የማወያየት ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ያሉ ቢሆንም በመቱ ዩኒቨርስቲ የተወሰኑ ተማሪዎች ውይይት ያለመፈለግ አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡

• ከሰሞኑ አንፃር ሲታይ በጅማ፣ መደወላቡ፣ መቱ፣ ወለጋ፣ ደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲዎች ሰላማቸው እጅጉን ተሻሽሏል፡፡

• በደብረታቦር ዩኒቨርስቲና ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ ላይ ዛሬ በከፊል ተማሪዎች ክፍል ያለመግባት ሁኔታ ያጋጠመ ሲሆን ከነዚህ ውጪ ባሉት ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የመማር ማስተማር ስራው በሰላማዊ ሁኔታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

እስካሁን ለተመዘገበው መሻሻል የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች፡-

• በዩኒቨርስቲዎች የፀጥታ ሀይል በተቀናጀና በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሠራ የተደረገ መሆኑ

• በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፉ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆኑ

• በዩኒቨርስቲዎቹ ያሉ የተማሪዎች ህብረት ተማሪዎቹን እያረጋጉ መፍትሄ እያመጡ መሆኑ

• የሃሰት መረጃዎች መበራከትን ለመከላከል ዩኒቨርስቲዎችና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ለሚዲያ ክፍት ማድረጋቸው ሲሆን

የህግ ማስከበር በተለይም ተጠርጣሪዎችን የመለየት እና ለህግ እንዲቀርቡ የማድረግ ስራው በሚመለከታቸው አካላት ተጠናክሮ መቀጠሉን እየገለፅን ከነዚህ ውጪ በየትኛውም ዩኒቨርስቲዎች የደረሰ ምንም አይነት ሌላ ክስተት አለመኖሩን እንገልፃለን፡፡

ከተማሪዎች ጋር የሚደረጉ ውይይቶችን ተከትሎ አበረታች የሆኑ መረጋጋቶች እየመጡ ነው፡፡ እነዚህም በቶሎ ወደ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ሁኔታ እንደሚቀየሩ እምነት አለን፡፡ ስለሆነም የተማሪዎች ቤተሰቦችም ሆኑ ህብረተሰቡ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ይሄንን በመገንዘብ ተማሪዎቹን የማረጋጋት ስራቸውን እንዲቀጥሉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ሁሉም የሚዲያ አካላት ትክክለኛ የሆነውን መረጃ ብቻ ለህብረተሰቡ በማድረስ ለዩኒቨርስቲዎቻችን ሰላም የበኩላቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

ህዳር 04/2012 ዓ.ም

Report Page