#ETH

#ETH


ዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ዎሕዴግ) በጥቅምት 30 2012 በጉታራ አዳራሽ ባዘጋጀው ህዝባዊ ውይይት መድረክ በአምስት አጀንዳዎች ከህዝብ ጋር በማወያየት ባለአምስት ነጥብ አቋም መግለጫ አውጥቷል።

የዎላይታ ህዝብ በኢትዮጵያ ሀገር ሆና ከተመሰረተችበት በርካታ አመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። አሁንም በሀገራችን ለሚታየው ለውጥና ከለውጡ ጋር ለሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋር በመሆን የሚያስከፍለውን ዋጋ የከፈለና እየከፈለ ያለ ህዝብ እና እንዲሁም በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የበለጠ መስዋዕትነትን መክፈሉን ሚዛናዊ አመለካከት ከተቃኘ ማንም ግለሰብና ህዝብ የሚገነዘበው ነው፡፡ 

የዎላይታን ህዝብ ባለታሪክና ዝነኛ፣ አቃፊ ህዝብ፣ አብሮነትን የሚያከብር፣ በእኩልነትና ነጻነት የማይደራደር፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳስብና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን የሰለጠነ ህዝብ መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ሀቅ ነው። የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲዊና ህገ መንግስታዊ መብትን ለማረጋገጥ፣ በእኩል ተጠቃሚነትና እኩል ተሳትፎ የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ብርቱ ትግል እያደረገች ትገኛለች።

እነዚህንና የመሳሰሉትን ሰፊ ውይይት በኃላ የተደረጉ የአቋም መግለጫዎች ፡-

1. የዎላይታ ህዝብ የህልውና ጉዳይ የሆነው ራስን በራስ የማስተዳደር የክልል ጥያቄ ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በመሆኑ ለክልል ምክር ጥያቄው ከቀረበ አንድ ዓመት የሚሞላው በታህሳስ 10/2012 ስለሆነ በሁሉም መንግድ ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈልና ለማሳካት ተስማምተናል።

2. በሎካ አባያ በኩል ለሲዳማ ያለአግባብ ይሰጣል በተባሉ 8 መንደሮች ላይ ምንም አይነት የህዝበ ውሳኔ እንቅስቃሴ እንዳይደረግና የዎላይታን ድምበር እንዲከበር እየጠየቅን የዎላይታ ዞን መንግስትም ይህንን አስመልክቶ ለህዝብ ይፋዊ መግለጫ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።  

3. በሰላማዊ አከባቢዎችና በዎላይታ የታወጀው ኢ-ህገመንግስታዊ ኮማንድ ፖስት የዜጎችን ዴሞክራሲዊ እንቅስቃሴን ክፉኛ የጎዳ የዜጎችን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ማዕቀብ መጣል ተገቢ ስላልሆነና ዜጎችን ዴሞክራሲዊ መብት የገደበ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲነሳ እንጠይቃለን። 

4. የዎላይታንና ሌሎችንም የብሔር ብሔረሰቦችን ማንነት፣ ባህልና እሴቶችን በዴሞክራሲዊ መንገድ ለመግለፅ ፌዴራልዝም አማራጭ የማይገኝለት መንገድ ስለሆነ በፌዴራልዝም እንደማንደራደር እንገልጻለን።

5. የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ዎሕዴግ) የዎላይታ ህዝብ ድምጽ ሆኖ በሚያደርገው ጉዳዮች፣ በሚያቀርባቸው ህገ መንግስታዊ ጉዳዮችና በዎላይታ ህዝብ በሚያደርገው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ከጎኑ ሆነን ትግሉን እንደምንደግፍ ቃል እንገባለን።

ጥቅምት 30 2012 ዓ.ም

ዎላይታ ሶዶ


Report Page