#ETH

#ETH


አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ በለጠ ካሳን ጨምሮ በሌሎች የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮችና አባላት ላይ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ፤

*

ከሰኔ 15ቱ የአማራ ሕዝብ መሪዎች እና የአገሪቱ ከፍተኛ የጦር መኮነኖች ግድያ ጋር በተያያዘ ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል በፖሊስ ተይዘው ከአራት ወራት በላይ በእስር ላይ የሚገኙትና በሃምሳ አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ መዝገብ ስር የቅድመ ክስ ምርመራ ከተከፈተባቸው 13 ተጠርጣሪዎች መካከል የተካተቱት:-

1ኛ) ክርስቲያን ታደለ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

2ኛ) በለጠ ካሳ የአብን ፅሕፈት ቤት ኃላፊ

3ኛ) አስጠራው ከበደ የአብን አባል

4ኛ) ሲሳይ አልታሰብ የአብን ብሔራዊ ም/ቤት አባል

5ኛ) ፋንታሁን ሞላ የአብን አባል

6ኛ) አማረ ካሴ የአብን የአዲስ አበባ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

7ኛ) አየለ አስማረ የአብን አባል

ላይ አቃቤ ሕግ የቅድመ ምርመራ ክስ መዝገብ ከፍቶ አሉኝ ያላቸውን 40 ምስክሮች በዝግ ችሎት ለመስማት ለ3ኛ ጊዜ ዛሬ ኅዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም ቀርበው ነበረ፡፡ አቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች ለደህንነታችን ስለምንሰጋ በተጠርጣሪዎቹ ላይ አንመሰክርም ስላሉኝ በአብን አባላትና አመራሮች ላይ የቅድመ ክስ ምርመራ ምስክሮችን እንደማያሰማ ገልፆ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰረት አድርጎ ክስ ለመመስረት ከአሁን ቀደም በመዝገቡ 1ኛ ተከሳሽ ሃምሳ አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ላይ ያቀረባቸው ምስክሮች ቃል ተገልብጦ እንዲሰጠውና መዝገቡ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲላክለት ጠይቋል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ ልመስርት ብሎ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 መሰረት ተጨማሪ 15 ቀን እንዲሰጠው ካስፈቀደ በኋላ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንዲሁም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሰጥቷቸው በነበሩ ትእዛዞች የዋስትና መብታቸው ይከበር እያለ እንደ ገና ተመልሶ ወደ ቀዳሚ ምርመራ ይመለሥ የሚለው ሥነ-ሥርዓታዊ አይደለም በሚል ተቃውሞ አቅርበው እንደነበርና የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ቀደሚ ምርመራ በምን ሥርአት ይቀርባል የሚለውን በግልፅ ያስቀመጠ ስላልሆነ በሚል ፍርድ ቤቱ ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ክርክሩ እንዲቀጥል በመፍቀድ የቅድመ ክስ ምርመራ የምስክሮችን ቃል ለመስማት ለ3 ጊዜ ያክል ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን በማስታወስ አቃቤ ሕግ በደንበኞቻቸው ላይ አሉኝ ያላቸውን ምስክሮች በተሰጠው 3 የጊዜ ቀጠሮ ሳያቀርብ ክስ ለመመስረት መዝገቡ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይላክልኝ ብሎ መጠየቁ ሥነሥርዓታዊ አለመሆኑንና በአቃቤ ሕግ የተንዛዛ አሰራር ደንበኞቻቸው የተፋጠነ ፍትሕ እንዳያገኙ እንቅፋት መሆኑን በመጥቀስ የተቃወሙ ሲሆን የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸውም ጠይቀዋል፡፡ አቃቤ ሕግ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ሊወጡ አይገባም ሲል ተቃውሟል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለአርብ ኅዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ላይ ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

(NMA)

Report Page