#ETH

#ETH


የሐሰት ዜናዎች


የሐሰት ዜናዎች ጉዳይ (በተለይ ደግሞ በሶሻል ሚዲያ) አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሰዎች የዜና ምንጮችን ሳያጣሩ በመጻፍ እና በማጋራታቸው ምክንያት ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል። ሰዎች በሐሰት ዜናዎች ተጣልተው ለመፈናቀል ደርሰዋል። ብዙዎች የአእምሮ ሰላማቸውንም አጥተዋል። መንግሥትም ቢሆን የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እና ፓናሎችን ከማዘጋጀት አልፎ፥ በሚዲያ የሚሠራጩ ዜናዎችን ይዘት በተመለከተ ሕግ እያዘጋጀ መሆኑን እየሰማን እንገኛለን። እኔም ደግሞ የበኩሌን ድርሻ መወጣት ስለፈለግኩ ራሳችሁን ትጠብቁበት ዘንድ አንዲት አጠር ያለች ጽሑፍ ለማዘጋጀት አሰብኩ፡፡ ይህቺ ጽሑፍ አቅጣጫ ለመጠቆም ያህል ብቻ የተከተበች ሲሆን – ስለ ሐሰት ዜናዎች ምንነት፣ አይነት፣ እና ደግሞ ራሳችሁን የሐሰት ዜና ሰለባ ከመሆን (አልፎም ሐሰተኛ ዜናዎች እንዲሰራጩ ከመርዳት) እንድትታደጉ ጠቋሚ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የውሸት ዜናዎችና የሶሻል ሚዲያው አብዮት

ዓለማችን ወደ ቴከኖሎጂው አብዮት ከገባች ወዲህ ዓለምን የበለጠ ለማቀራረብ እና የመረጃ ልውውጥን ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ሆኖም ግን ከእነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ውስጥ የሶሻል ሚዲያን ያክል ገንኖ የወጣ አልፎም ደግሞ ዓለምን ይበልጥ ያቀራረበ አይገኝም፡፡ የሶሻል ሚዲያ እጅግ አይሎ ከመውጣቱም የተነሳ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች ‘የሶሻል ሚዲያ አብዮት’ ብለው ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የሶሻል ሚዲያ ለብዙ ጊዜ የተጠፋፉ ሰዎችን ሲያገናኝ፥ ወንጀለኞችን ለፍርድ ሲያቀርብ አልፎም ደግሞ(እንደ ግብጽ ባሉ ሀገራት) መፈንቅለ መንግሥትን ጭምር ሲያቀላጥፍ ተመልክተናል፤ በእኛ ሀገርም ቢሆን ለለውጡ መካሄድ የማይናቅ ሚና ተጫውቷል። እነዚህን ሁሉ ስንመለከት እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ያሉ ሶሻል ሚዲያዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ በቀላሉ ችላ የማይባሉ መሆናቸውን እናጤናለን፡፡

ይህ የሶሻል ሚዲያ አብዮት ከተፈጠረ በኋላ ብዙ እክሎችና ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ ከእነዚህ መካከል ዋናዎቹን ትዊተር እና ፌስቡክ ብናይ ስንኳ፡- ትዊተር ለአይሲስ የሽብር ምልመላ እንቅስቃሴ በመዋሉ ሲተች ፌስቡክ ደግሞ በተለይም በቅርቡ እንደታዘበነው የሰዎችን የግል መረጃ ለደህንነት አካላት አሳልፎ በመስጠት ክስ ቀርቦበታል፡፡ ሆኖም ግን የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ ከእለት እለት አሳሳቢ አየሆነ የመጣው ሌላው ተግዳሮት ‘የውሸት ዜናዎች’ ስርጭት ነው፡፡ በሀገራችንም ቢሆን በሶሻል ሚዲያ የሚሰራጩ የውሸት ዜናዎች ለብዙዎች ሰላም መደፍረስ ምክንያት ሆኗል፡፡ የታይዋን መንግሥት የውሸት ዜናዎች – በተለይም ስለ አካባቢዋ እና ፖለቲካ ቀጠናው የሚሰራጩት- በማኅበረሰቡ ላይ የሚፈጥሩት ችግር እጅግ ስላሳሰባት በየትምህርት ቤቱ የሐሰት ዜናዎችን እንዴት መለየት እንደሚቻል የሚያስተምር አዲስ የትምህርት ካሪኩለም ቀርጻ ሥራ ላይ አውላለች፡፡[1] ይህ ከሆነ ታዲያ ሁላችንም የውሸት ዜናዎችን ባህሪይ በማወቅ ራሳችንን እና የአእምሮ ሰላማችንን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

የውሸት ዜና ምን ማለት ነው?

የውሸት ዜና ማለት ሆን ተብለው የሚፈጠሩ፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ደግሞ በኅትመት ወይም በሶሻል ሚዲያ የሚሰራጩ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያዎች ናቸው፡፡[2] የውሸት ዜናዎች ሲፈጠሩ ሰዎችን ለማሳሳት፣ ለአመጽ ለማነሳሳትም ሆነ ለማወናበድ ታስበው ሲሆን፣ የተለያዩ መንግሥታትም የህዝብን ሃሳብና የተቃውሞ አቅጣጫ ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት ተጠቅመውታል፡፡ ከዚህ ቀደም የውሸት ዜናዎችን ማሰራጨት ከባድ የነበር ቢሆንም፣ በተለይም የሶሻል ሚዲያው አብዮት ከተከሰተ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ስርጭቱ ጨምሯል፡፡[3] በመረጃ መዋቅር ውስጥ ብንመለከት፣ ሰባት አይነት የውሸት ዜናዎች ማውጣት ይቻላል[4]፡-

1. ሳታየር/ፉገራ [Satire/Comedy] – ይህ አይነት የውሸት ዜና በሌላ አጠራር ‹ኩምክና› የምንለው ሲሆን፣ ሰዎችን ከማሳቅ እና ከማዝናናት ውጪ ሌላ አይነት ዓላማ የለውም፡፡ ዜናውን የሚፈጥሩትም ሆነ የሚያሰራጩት ሰዎች ዋና አላማቸው ሰዎችን ለማዝናናት፣ አለፍ ሲልም በኮሜዲ እውቅና ለማግኘት ነው፡፡

2. አሳሳች የመረጃ ይዘቶች [Misleading Content] – እነዚህ መረጃዎች ደግሞ ሰዎች ትክክለኛውን መረጃ እንዳያገኙ ታስቦ ለማሳሳት የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ትክክለኛ መረጃዎችን በማጣመም አንድን ሰው ወይም ተቋም ተጠያቂ ለማድረግ ሲሞከርም ይታይበታል፡፡

3. አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች [Imposter Content] – እነዚህ ደግሞ የዜና/መረጃ ምንጭ በመሆን የሚያገለግሉ ሰዎችን ወይም ደግሞ የዜና ተቋማትን በመምሰል/በማስመሰል የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት የሚሞክሩ ናቸው፡፡

4. የፈጠራ ወሬ [Fabricated Content] – ይህ ደግሞ ዜናው/መረጃው ከኋላው ምንም አይነት የእውነታ መሠረት የሌለው እና መቶ በመቶ የፈጠራ የሆነ ወሬ ነው፡፡ ይህም ብዙዎችን ለማታለል ወይም ለመጉዳት ታስቦ የሚፈጠር ነው፡፡

5. ሐሰተኛ ግንኙነቶች [False Connections] – ይህ ደግሞ የሚሆነው የዜናው/መረጃው ርዕስ የሚጠቁመው ነገር ሌላ ሆኖ ሳለ ከውስጥ ያለው ፍሬ ነገር ግን ከርዕሱ ጋር ፍጹም የማይገናኝ ሲሆን ነው፡፡ በውጪው ዓለም እንዲህ የሚያደርጉ የዜና አውታሮች ያሉ ሲሆን፣ ሰዉን ሊስብ የሚችል አርዕስት ይለጥፉና ከውስጡ ያለው ግን ፍጹም ከርዕሱ ጋር የማይገናኝ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያም ቢሆን በብዙ ቪዲዮዎች ላይ ይስተዋላል፡፡

6. ሐሰተኛ ዐውድ [False Context] – በዚህ ጊዜ ዜናው/መረጃው ትክክለኛ እና ተዓማኒ ሆኖ ሳለ፣ የገባበት ወይም የተተረጎመበት ዐውድ ግን ፍጹም የተሳሳተ ሲሆን ነው፡፡ በአብዛኛው ዐውድ አረዳዳችንን ስለሚወስን፣ ምንም እንኳን መረጃው እውነተኛ ቢሆን የገባበት ዐውድ ከተሳሳተ ግን የምንሰጠውም ትርጓሜ የተሳሳተ ይሆናል፡፡

7. የተጣመመ መረጃ [Manipulated Content] – አንድ እውነተኛ መረጃ ሰዎች በተሳሰተ መንገድ እንዲረዱት ተደርጎ ሲጣመም በዚህ ጎራ ውስጥ ይካተታል፡፡ መረጃውን በመቆራረጥ፣ ቆርጦ በመቀጠል ወይንም ቅድመ-ተከተሉን በማዛባት ሊደረግ ይችላል፡፡

የሐሰት ዜናዎች ለምን ይፈጠራሉ?

ፈርስት ድራፍት [First Draft] በተሰኘው ድረ-ገጽ ላይ የሚዲያ ተንታኝ እና ባለሞያ የሆነችው ክሌር ዋርድል እንደምትገልጸው ከሆነ፣ የሐሰት ዜናዎች ስርጭት ምክንያት በስምንት ሊከፈል ይችላል፡፡ ስምንቱን ምክንያቶች ከላይ ከተጠቀሱት የሐሰተኛ ዜና ዓይነቶች ጋር ስናገናኛቸው ደግሞ ጥሩ አረዳድ ይኖረናል፡፡ እነርሱም፡-

1. ደካማ ጋዜጠኝነት [Poor Journalism] – በደካማ ጋዜጠኞች – ማለትም ተገቢውን የሙያ ሥነ-ምግባር ተከትለው ዜናዎችን በአግባቡ የማያጣሩ – ምክንያት ሐሰተኛ ግንኙነቶች (የማይገናኘውን ማገናኘት)፣ አሳሳች የመረጃ ይዘቶች (ምንጭን ካለማጣራት) እና ሐሰተኛ ዐውድ (በጥልቀት ካለማጣራት የተነሳ ባልተገባ ዐውድ መተርጎም) ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡

2. ሰዎችን ለመኮመክ [To Parody] – ይህ ለቀልድ/ሰዎችን ለመኮመክ ተብለው ሳታየር/ኮሜዲ ዜናዎች፣ አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች እና የፈጠራ ወሬ ሊከሰት ይችላል፡፡

3. ሰዎችን ለማተራመስ/ለማናደድ [To Provoke/Punk] – ሰዎችን ለማተራመስ/ለማናደድ ዓላማ የሚነሱ ሰዎች ደግሞ ከላይ ካየናቸው መካከል አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች፣ የተጣመመ መረጃ እና የፈጠራ ወሬን ይጠቀማሉ፡፡

4. ከፍተኛ ፍላጎት [Passion] – ይህ ደግሞ ዜናዎችን ለሌሎች ለማጋራት ከሚኖር ከፍተኛ ጉጉት ወይም ፍላጎት የሚመነጭ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ዜናዎችን የሚያጋሩ ሰዎች ሐሰተኛ ዐውድ ያጠቃቸዋል፡፡ ይህም ማለት ለማጋራት ከመቸኮል የተነሳ መረጃው ሊተረጎምበት የሚገባውን ዐውድ ባለማጤን ለሰዎች ያጋራሉ፡፡

5. ጭፍን ድጋፍ [Partisanship] – ይህ ደግሞ ለአንድ ግለሰብ ወይንም ተቋም ከሚኖራቸው ጭፍን ድጋፍ (አንዳንዴም ጭፍን ጥላቻ) የተነሳ አሳሳች የመረጃ ይዘቶችን (የሚወዱትን ተቋም ከጥቃት ለመከላከል ወይም የሚጠሉትን ለማጥቃት) እና ሐሰተኛ ዐውድ (ከተገቢው ዐውድ ውጪ ለራሳቸው እንደሚያመች አድርገው በመተርጎም) ይጠቀማሉ፡፡

6. የገንዘብ ትርፍ [Profit] – አንዳንድ ሰዎች ወይም ተቋማት የሰዎችን እይታ ለመሳብ ሲባል፣ የሕትመት ሚዲያ ባለሞያዎችም ሕትመቶቻቸውን ለመሸጥ እንዲያመቻቸው ሐሰተኛ ግንኙነቶችን (የሚገናኘውን ከማይገናኘው በማቀናጀት፣ በተለይም ውስጥ ካለው ፍሬ ነገር የማይገናኝ ሳቢ የሆነ ርዕስ በመስጠት)፣ አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶችን (ተዓማኒነት ያላቸውን ተቋማት ማንነት በመስረቅ/በማስመሰል) እና የፈጠረ ወሬዎችን (የሰዎችን እይታ ለመሳብ) የመጠቀሙ እድል አላቸው፡፡

7. የፖለቲካ የበላይነት [Political Influence] – አንዳንድ ሰዎች ወይም ተቋማት የፖለቲካ የበላይነትን ለማግኘት ሲሉ፣ ሐሰተኛ የመረጃ ይዘቶችን (ራሳቸውን መልካም ሌሎችን ክፉ ለማስመሰል)፣ ሐሰተኛ ዐውድ (ለራሳቸው የፖለቲካ ፍጆታ እንዲመች በማድረግ ያልተገባ ዐውድ ለመረጃዎች በመስጠት)፣ የተጣመመ መረጃ (ቆርጦ በመቀጠል፣ ቅድመ-ተከተሎች በማዛባት) እና የፈጠራ ወሬ (ሌሎችን የበታች ራሳቸውን የበላይ ለማድረግ) ይጠቀማሉ፡፡

8. ፕሮፓጋንዳ [Propaganda] – አስቀድሞ የቃሉን ምንነት ለማየት፣ ፕሮፓጋንዳ ማለት የሰዎችን ድጋፍ ለማግኘት ወይም ደግሞ አንድን አጀንዳ ለማራጋብ እንዲያመች በማድረግ እውነታን በመቆነጻጸል እና የሰዎችን ስሜታዊነት ለግል አጅንዳ ፍጆታ ለማዋል ታስቦ የሚሰራጭ መረጃ ነው፡፡[5] በዚህ መሠረት በፕሮፓጋንዳ ሰዎችን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ አካላት አሳሳች የመረጃ ይዘቶች፣ ሐሰተኛ ዐውድ፣ አጭበርባሪ የመረጃ ይዘቶች፣ የተጣመመ መረጃ እና የፈጠራ ወሬን ይጠቀማሉ፡፡

ጠቅላላ መፍትሔዎች ምንድር ናቸው?

የሐሰተኛ ወሬዎችን ምንነት፣ ምንጭ እና ዓይነት ከተገነዘብን ዘንዳ ራሳችንን እንዴት ከሐሰተኛ ወሬዎች መጠበቅ እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ይህንን በተመለከተ በሁለት መልኩ ማየት ተገቢ ነው፤ የመጀመሪያው ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዴት መለየት እንደምንችል ማወቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እንዴት መግታት እንደምንችል መገንዘብ ይሆናል፡፡

የመጀመሪያው ሐሰተኛ መረጃዎችን አንዴት መለየት እንደምንችል ማወቅ ይገባናል፡፡ ይህንን በተመለከተ ደግሞ “International Federation of Library Associations and Institutions” የተሰኘው ተቋም ባሳተመው መረጃ ላይ ስምንት የተለያዩ መንገዶችን ይጠቁመናል፡፡

የመጀመሪያው በማንኛውም ወቅት አንድን ዜና ስናነብብ/ስንመለከት “ምንጩ ምንድር ነው?” ብለን በጥልቀት ማሰብ ነው፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያ ወይንም ሬዲዮ ከሆነ ተዓማኒነታቸውን (በተለይም ለዜናው ዋቢ መጥቀሳቸውን) በማጤን፣ ድረገጽ ከሆ ደግሞ ድረገጹን በመቃኘት እና በዝርዝር የተቀመጡ ራዕይ እና ግቦቹን በመመልከት፣ በተጨማሪም ስልክ፣ ኢሜይል፣ የመልእክት ሳጥን ቁጥር ካላቸውም እውነተኛነቱን ማጣራት ይገባናል፡፡

በሁለተኛነት ደግሞ ለዜናዎች የሚሰጡ አርዕስቶች የሰዎችን ቀልብ ለመሳብ ታስበው ሊጻፉ ይችላሉና፣ ከርዕሱ ባለፈ ውስጠ ነገሩን በደንብ መመርመር እና ማጤን ይገባናል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ጸሐፊውን ማጣራት ነው፡፡ የዜናው ጸሐፊ ማነው? እውነተኛ ሰው ነው ወይስ የሐሰት ማንነት? — የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ እውነትነቱን ማጣራት ይገባል፡፡

በአራተኛ ደረጃ ምንጮችን በሚገባ መመርመር አለብን፡፡ መረጃዎች ተጠቅሰዋል? መረጃዎች ከተጠቀሱስ አስተማማኝነታቸው ምን ያህል ነው? በተለይም ድረገጽ ከሆነ የተጠቀሰውን ዋቢ ጭምር በመመርመር ማጣራት ይኖርብናል፤ አልፎም ደግሞ “የተጠቀሱት ማስረጃዎች እውነት የዜናውን ፍሬ ነገር ይደግፋሉ?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡

አምስተኛው ደግሞ ቀኑን ማጣራት ነው፡፡ አልፎ አልፎ ያለፈባቸው ዜናዎችን በመቆነጣጠር የሚጠቀሙ አካላት አሉና “ይህ ዜና የተነገረው/የተጻፈው መቼ ነው?” በሚል ማጣራት ይኖርብናል፡፡

ስድስተኛው “ቀልድ ይሆን?” ብለን ራሳችንን መጠየቅ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው “ሳታየር/ኮሜዲ” በተባለው ዘውግ የሚካተቱና ሰዎችን ለማሳቅና ለማዝናናት ታስበው የሚለቀቁ ዜናዎች ስላሉ ቀልድ የሆነውን እውነት ከሆነው እንዳናምታታ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

ሰባተኛው የራሳችንን አመለካከቶች ማገናዘብ ነው፡፡ “ይህንን ዜና እኔ ባልተገባ ሁኔታ እየተረዳሁት ይሆን?”ብለን አመለካከቶቻችን የሚፈጥሩብንን ተጽእኖ መለየት ይኖርብናል፡፡ የመጨረሻው ደግሞ በዙሪያው ጥሩ እውቀት ያላቸውን ሰዎች መጠየቅ ነው፡፡ በተለይም የጉዳዩ ትንተና ከእኛ አቅም በላይ እንደሚሆን ከገባን፣ በጉዳዩ ዙሪያ ጥሩ እውቀት ያላቸውን መጠየቁ እና ከእነርሱ መረዳቱ መልካም ይሆናል፡፡

የሶሻል ሚዲያ ዜናስ?

በሚዲያ ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎች እንደሚመክሩን ከሆነ ሰዎች በእለት/በሳምንት ማግኘት ያለባቸውን ዜና እንደ ፌስቡክ እና ትዊተር ካሉ ሶሻል ሚዲያዎች ማግኘት አይገባቸውም፡፡ የዚህም ምክንያት በሶሻል ሚዲያ የሚሰራጩ ዜናዎች እውነት ወይም ውሸት መሆናቸውን ለመለየት የሚከብዱ ስለሆኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን አንድ ሰው “እኔ ዜናዎችን ከፌስቡክ እና ሌሎች ሶሻል ሚዲያዎች ማግኘት እፈልጋለሁ” የሚል ከሆነ አንዳንድ የጥንቃቄ እርምጃዎች ቀርበዋል።[6]

በሶሻል ሚዲያ ዜናዎቻችንን የምናገኝ ከሆነ፣ የመጀመሪያው ጥንቃቄ እርምጃ ዜናዎችን መምረጥ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ስለ ሁሉም ነገር ማወቅ የማይታሰብ በመሆኑ በምንፈልጋቸው አርእስት ዙሪያ ብቻ ያሉትን መርጠን ማንበብ ይኖርብናል፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በሶሻል ሚዲያ የምንወዳጃቸውን ሰዎች መምረጥ ነው፡፡ መረጃን የሚወዱ፣ ጥሩ ትንተናን የሚሰጡ እና ለእውቀት ፍላጎት ያላቸው፤ አልፎም ደግሞ የበለጠ እንድናስብ እና እውቀትን እንድንገበይ የሚያደርጉንን ሰዎች መወዳጀቱ ጥሩ ነው፡፡ የዚህ ሌላኛው ጥቅም ደግሞ አዋዋላችን ከእንደዚህ አይነት ሰዎች ጋር ከሆነ እኛም የአስተሳሰብ ምህዳራችንን እንድናሰፋ እድልን ይሰጠኛል፡፡

ሦስተኛው ደግሞ በሶሻል ሚዲያ ዜናን የሚያሰራጩ ታማኝ ምንጮችን ማግኘት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ “እንዲህ ተፈጠረ!” አይነት የወከባ ዜናን ሳይሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያ በእውቀት የዳበረ ትንተናን የሚሰጡ ሰዎችን ፈልጎ መወዳጀት ይመከራል፡፡ ይህንን ካደረገን ተዓማኒነት ያለው ዜና ማግኘት ብቻ ሳይሆን የበለጠ እውቀትንም እንድናዳብር ምክንያት ይሆነናል፡፡

በአራተኛ ደረጃ ደግሞ “ቅንጭብጭብ” መረጃዎች ላይ ከማተኮር የበለጠ ዜናዎቻችንን በማንበብ ማግኘቱ ይመከራል፡፡ ይህም ማለት የሕትመት ሚዲያዎችን (ጋዜጤዎች፣ መጽሔቶች…) ማንበብ ላይ ብናተኩር ተዓማኒነት ያላቸውን ዜናዎች የማግኘት እድላችን የሰፋ ይሆናል፡፡

የሐሰት ዜናዎችን ለመግታት ምን ማድረግ አለብን?

በእውቁ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ማዕከልነቱን ያደረገው ጋዜጠኛ እና የዲጂታል ጋዜጠኝነት ባለሞያ ክሬይግ ሲልቨርማን ባደረገው ጥናት መሰረት [7] የሐሰት ዜናዎች ከማስተባበያ ዜናዎች በበለጠ ፍጥነት እንደሚሰራጩ ታውቋል፡፡ ይህ ማለት አንድ የሐሰት ወሬ ከተሰራጨ በኋላ እርሱን ለማስተበል ከሚሰራጭ ሌላ ዜና አንጻር የሐሰት ዜናው የበለጠ የስርጭት ምህዳር አለው ማለት ነው፡፡ ይህ ከሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የውሸት ዜናው እንዳይሠራጭ አስቀድመው የራሳቸውን አስተዋጽኦ መወጣት አለባቸው ማለት ነው፡፡

የመጀመሪያው የሁላችንን ድርሻ በተመለከተ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌስቡክ የሚሰራጩ የሐሰት ወሬዎች አስቸጋሪ የሆነ ደረጃ ላይ ስለደረሱ፣ ፌስቡክ የውሸት ዜናዎችን የምንጠቁምበትን ስርዓት አደራጅቷል፡፡ በዚህ መሰረት አንድን የሐሰተኛ ዜና ካገኘን (ሐሰተኛ መሆኑንም ካረጋገጥን) ሪፖርት ማድረግ እንችላለን፡፡ ሪፖርት ስናደርግም “It’s a false news story” የሚለውን በመምረጥ ሐሰተኛነቱን መጠቆም እንችላለን፡፡ በተጨማሪም ምስሎችን አስታኮ የሚሰራጭ የሐሰት ዜናም ካገኘን http://www.tinyeye.com የተሰኘውን ድረገጽ በመጠቀም ምስሎቹን ከትተን በኢንተርኔት ላይ ከየት ቦታ ላይ እንደተቀዱ ማጣራት እንችላለን፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጋዜጠኞችን ይመለከታል፡፡ ጋዜጠኞች በተቻለ መጠን የማጣሪያ መንገዶችን በመጠቀም የተጣራ ዜናን ለማድረስ መስራት አለባቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት እና የሚዲያ ተቋማት የዲጂታል ሚዲያ ትምህርትን [Digital Media Literacy] በማስፋፋት ተማሪዎች እና ብዙሃኑ ማኅበረሰብ የሐሰት ዜናዎችን የሚለይበትን መንገድ (አስፈላጊ ከሆነ አንደ ጃፓን ካሪኩለም ቀርጾ) ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በዚህ መልክ ሐሰተኛ ዜና ስርጭት እንዳያገኝ በማድረግ የተቻለንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን፡፡ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት የሐሰት ዜናዎችን መለያና መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን በተመለከተ ያጋራውን ምስል ከሥር አስቀምጫለሁ፤ ከላይ የተመለከትነውን አጠር ባለ መልኩ የሚገልጽ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።


የማጣቀሻ ጽሑፎች

[1] – Smith, Nicola (April 7, 2017). “Schoolkids in Taiwan Will Now Be Taught How to Identify Fake News”, Retrieved on Auguest 11, 2018 from http://www.time.com

[2] – Smith, Bruce L. (17 February 2016). “Propaganda” . Encyclopædia Britannica. Encyclopædia Britannica , Inc. Retrieved 26 March 2019.

[3] – Hunt, Elle (December 17, 2016). “What is fake news? How to spot it and what you can do to stop it”, Retrieved on Auguest 10, 2018 from http://www.theguardian.com

[4] – Wardle, Claire (February 16, 2017). “Fake news. It’s complicated.”, Retrieved on August 11, 2018 from http://www.firstdraftnews.org

[5] – Smith, Bruce L. (February 17, 2016). “Propaganda”. Encyclopedia Britannica, Inc. Retrieved on August 11, 2018 from http://www.britannica.com

[6] – Mattive, Nilus (March 9, 2018). “10 Tips for Filtering Out Fake News”, Retrieved on August 11, 2018 from http://www.dailyreckoning.com

[7] – Nyhan, Brendan(Sept 29, 2014). “Why Rumors Outrace the Truth Online”, Retrieved on August 11, 2018 from http://www.nytimes.com

ለተጨማሪ ንባብ

Edward S. Herman, Noam Chomsky – “Manufuacturing Consent: The Political Economy of Mass Media”.

Daniel Levitin – “Weaponized Lies: How to Think Critially in the Post-Truth Era”.

Jim Fingal, John D’Agata – “The Lifespan of a Fact”.

A Brad Schwartz – “Broadcast Hysteria: Orson Welles’s War of the Worlds and the Art of Fake News”.

(Fresenbet G.Y Adhanom)


Report Page