#ETH

#ETH


በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ምሽት 5፡00 አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የተማሪዎች ሕይወት አልፏል፡፡ በተወሰኑ ተማሪዎች ላይ ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ በተለይም ለአብመድ መግለጫ የሰጡት የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የአካደሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት እና ተወካይ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስረስ ንጉሥ ‹‹ምሽት አካባቢ የተፈጠረው ችግር ምንጩ እስከሚጣራ ድረስ ከመገመት የዘለለ በትክክል አይታወቅም›› ብለዋል፡፡ በግጭቱ የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉን እና በስምንት ተማሪዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የተናገሩት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በወልድያ አጠቃላይ ሆስፒታል ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

‹‹በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ሃይማኖትን በመስበክ እና ወደ ግጭት የሚያመሩ እንቅስቃሴዎችን ሲያካሂዱ የነበሩ ተማሪዎች በሥነ ምግባር ግድፈት ከትምህርት ገበታ መታገዳቸው እና በሰሞኑ በሀገሪቱ የነበረው የፖለቲካ ችግር መነሻ ሊሆኑ እንደሚችሉ እንገምታለን›› ያሉት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ ትክክለኛ ችግሩ ተጣርቶ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ከጉዳቱ በኋላ ከተማሪ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገን መግባባት ላይ ደርሰናል›› ያሉት ዶክተር አስረስ ተማሪዎች ተማሪዎች ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ በማሳሰብ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ እና ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ተማሪዎቹ በተወካዮቻቸው አማካኝነት የፀጥታ እና ደኅንነት ስጋት ስላለባቸው ዋስታና እንዲያገኙ ጠይቀዋል›› ያሉት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ ‹‹የመከላከያ ኃይል ወደ ግቢው እንዲገባ እየተነጋገርን ነው፤ ማምሻውንም ወደ ግቢያችን ይገባል›› ብለዋል፡፡

በደረሰው ጉዳት በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለፁት ዶክተር አስረስ ‹‹ጦማሪያን፣ አክቲቪስቶች እና የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት በስብጥርና በፍቅር ተንሰላስሎ የሚኖረውን ማኅበረሰብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ጥረት ሊያቆሙ ይገባል›› ብለዋል፡፡

(AMMA)

Report Page