#ETH

#ETH


ወልዲያ ዩኒቨርስቲ በተከሰተው የአማራ ማስሚዲያ ኤጀንሲ ተከታዩን ዘገባ ሰርቷል!

ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ወደነበረበት ሠላማዊ ሁኔታ እየተመለሠ መሆኑ ተገልጿል፡፡በወልድያ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ምሽት ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ጉዳት ደርሷል፡፡ትናንት ከምሽቱ 4፡00 እስከ 5፡00 ገደማ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉና ስምንት ተማሪዎች ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት እንዳጋጠማቸው ተገለጸ፡፡ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንኤ መኮንን ለአብመድ በስልክ እንደገለጹት ምሽት ተማሪዎች ኳስ በቴሌቪዝን በጋራ ሲከታተሉ አምሽተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት ነው የተማሪዎች ሕይወት ያለፈውና የአካል ጉዳት ያጋጠመው፡፡

ጉዳት ካጋጠማቸው ስምንት ተማሪዎች ሦስቱ ቀላል ጉዳት ያጋጠማቸው ስለነበር መጠነኛ ሕክምና አግኝተው ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለሳቸውንም አቶ ወልደትንሳኤ አስታውቀዋል፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎችንና የተማሪ ተወካዮችን በችግሩ ዙሪያ ማወያዬታቸውን ያመለከቱት አቶ ወልደትንሳኤ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለመያዝና ለሕግ ለማቅረብ እየተሠራ እንደሆነ አስውቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውና የአካባቢው አስተዳደር የተማሪዎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ እየሠሩ እንደሚገኙ ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው ‹‹ከዚህ በፊት የግጭት ምንጭ የሚሆኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲፈቱ በትኩረት ሠርተናል፤ የውኃ፣ መብራትና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲቀረፉም እየተደረገ ነው፤ ብዙ ውይይቶችም ተደርገዋል፡፡ የአሁኑ ግጭት መንስኤ ምን እንደሆነ ግን ገና እየተጣራ ነው›› ብለዋል፡፡ ‹‹የዞን አስተዳደሩና የዞኑ ሕዝብ በልጆቹ መነጠቅ አዝኗል፤ ለሁላችንም መጽናናቱን እንዲሰጠን እመኛለሁ፤ የተጎዱትም በቶሎ አገግመው ወደ ትምርታቸው እንደሚመለሱ ተስፋ አደርጋለሁ›› ብለዋል አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን ለአብመድ ሲናገሩ፡፡

የፀጥታ ኃይል በአካቢው መሠማራቱንና ተማሪዎች መረጋጋታቸውንም አስታውቀዋል፤ ተማሪዎች የእርስ በእርስም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር የሚኖሯቸውን ልዩነቶች በሰከነ መንገድ እንዲፈቱም አሳስበዋል፡፡ አብመድ ከተማሪዎች እንዳረጋገጠው ዩኒቨርሲቲው አሁን በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው፤ ተማሪዎቹ ተረጋግተው በቤተ መጻሕፍትና እና በመኖሪያ ክፍሎቻቸው እንዲሁም በግቢው እየተንቀሳቀሱ እና መደበኛ ተግባራቸውን እየከወኑ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

(አብመድ)

Report Page