#ETH

#ETH


የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 75ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ዝርዝርም እንደሚከተለው ቀርቧል፦

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ በአገራአችን የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊ አገራዊ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማደውረግ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የሪፎርም ሥራዎችን ለማከናወን እንዲቻል አዲስ አዋጅ ጸድቆ ሥራ ላይ መዋሉ ይታወሳል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ከተካተቱ አዳዲስ አደረጃጀትና መዋቅሮች ጋር ለማጣጣም፣ በስራ ላይ ባለው ደንብ የታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን ለማስተካከል፣ የመከላከያ ሰራዊቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የሚረዱ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ለማካተት በሚያስችልና የመከላከያ ሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸምና ሞራላዊ ዝግጁነት ለማጠናከር ሲባል የመከላከያ ሰራዊት ደንብ ቁጥር 385/2008ን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ም/ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን በአሁኑ ወቅት በተግባር ስራዎችን እያከናወነ ያለበት ሁኔታ ከተጣለበት ሃላፊነት እና አላማውን ከመፈጸም አኳያ የደንቡ አንዳንድ ክፍሎች ግልጸኝነትን ባለው መንገድ ያልተመላከቱ ስለሆነ የማቋቋሚያ ደንቡን ማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ የመከላከያ ሚኒስቴር ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ም/ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ደንቡ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

3. ሌላው ም/ቤቱ የተመለከተው የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርዓትን ለመደንገግ በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት መንግስታዊ አስራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ሃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን የተመለከተ በመሆኑ፤ የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃገብነት በሕግ የሚመራና ለህግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌዴራል የአስተዳደር ስነ-ስርዓትን ለመደንገግ ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

4.የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ሌላው በም/ቤቱ የታዬ ጉዳይ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሀገራዊ አንድነት ፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሃነት ጠንቅ መሆኑን በመገንዘብ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገራችን በህብረተሰቡ መካከል ያሉ የመልካም እሴቶች በጥላቻ ንግግሮችና በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ እየተሸረሸሩና ለሀገርም ስጋት የደቀኑ በመሆናቸው እንዲሁም እነዚህን ችግሮች አሁን ባሉት ህጎች መፍታት የማይቻል በመሆኑ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

5. በመጨረሻም ም/ቤቱ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ እና በጅቡቲ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ተቀብሎ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።


Report Page