#ETH

#ETH


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በመደገፍ ዛሬ በአምቦ ከተማ ሊካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ተሰረዘ። የድጋፍ ሰልፉ ሳይካሄድ የቀረው ሀሳቡን የተቃወሙ ወጣቶች ያሰራጯቸው መልዕክቶች ስጋት በመፍጠራቸዉ ነው ተብሏል።

ሰልፉ ለዛሬ የተጠራው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሐሙስ በአምቦ ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የገጠማቸው ተቃውሞ የከተማዋን ነዋሪ እንደማይወክል ለመግለጽ በሚል እንደሆነ ነዋሪዎች ለጀርመን ሬድዮ ተናግረዋል። ሰልፉ ይካሄዳል መባሉን ተከትሎ ዛሬ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ጀምሮ የኦሮሚያ ልዩ ፖሊሶች እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በአበበች መታፈሪያ ሆቴል እና በከተማይቱ ስቴድየም አካባቢ ተሰማርተው እንደነበር ነዋሪዎቹ ገልፀዋል። የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት እስከ ጠዋቱ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ በአካባቢው መቆየታቸውንም አክለዋል።

የዛሬውን የድጋፍ ሰልፍ የጠራው አካል በግልጽ ባይታወቅም ጥሪው ግን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወር መቆየቱን የጀርመን ድምፅ ሬድዮ ያነጋገራቸው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች አስረድተዋል። በኦሮሚያ ክልል ከሰሞኑ በተቀሰቀሰው ሁከት “የተጎዱ ወጣቶች ሆስፒታል ባሉበት እና የሟች ቤተሰቦችም ካሳ ባላገኙበት በዚህ ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ መካሄድ አይገባውም” የሚሉ ወገኖችም ተቃውሟቸውን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲያሰራጩ እንደነበርም ጠቁመዋል። ይህም በከተማይቱ ውስጥ ስጋት እና ፍርሃት በመፍጠሩ የዛሬው ሰልፍ ሳይካሄድ መቅረቱን ገልጸዋል።

የጀርመን ራድዮ ያነጋገራቸው ሁለት የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች የዛሬው የድጋፍ ሰልፍ የተጠራው "በመንግስት ካድሬዎች ነው" ብለዋል። ለዚህም ዛሬ ያጋጠማቸውን በማስረጃነት ጠቅሰዋል። ነዋሪዎቹ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ በከተማይቱ ባለው አበበች መታፈሪያ ሆቴል ፊት ለፊት በመንግስት መኪና "የሰልፍ ውጡ ቅስቀሳ ሲደረግ ተመልከተናል" ብለዋል። በተለምዶ "ሞንታርቦ" የሚባለውን የድምጽ ማጉያ የጫነው ይሄው ፒክ አፕ ተሽከርካሪ በተቃዋሚ ወጣቶች በደረሰበት የድንጋይ ውርጅብኝ የጎን መስታወቱ መሰበሩንም አስረድተዋል። ከጥቃቱ በኋላ ተሽከርካሪው አካባቢውን መልቀቁን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

አምቦ ጠዋት ላይ ከነበረው መጠነኛ ውጥረት ባሻገር የዕለት ተዕለት ሰላማዊ እንቅስቃሴዋን እያካሄደች እንደምትገኝ ነዋሪዎቿ ለጀርመን ሬድዮ አረጋግጠዋል። ሬድዮ ጣቢያው በአምቦ ሊደረግ ታስቦ ስለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ የከተማይቱ አስተዳደር ኃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት እንዳልተሳካለት ገልጿል።

(የጀርመን ድምፅ ሬድዮ)

Report Page