#ETH

#ETH


የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፓስፖርት በማውጣት ሂደት እየተስተዋለ የመጣው ሙስና እና ብልሹ አሰራር መፈትሄ እንዲበጅለት አሳሰበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲን የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ አፈፃፀሙን በሚመለከት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል።

በሪፖርቱ እንዳመለከተውም የፓስፖርት ክምችት ውስን በመሆኑ በአሰጣጥ ሂደቱ ችግሮች መስተዋላቸውን አመላክቷል።

ከፓስፖርት እጥረት ጋር ተያይዞ ችግሩ የተወሳሰበ መሆኑም ተገልጿል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜግነት መብት የሆነውን ፓስፖርት ለማውጣት ለወራት በቀጠሮ የሚጉላሉ እያሉ ጥቂቶች በአቋራጭ ሲወስዱ ይስተዋላል።

ይህ አሰራር የኅብረተሰቡን እሮሮ እያባባሰ መጥቶ በመንግስት ላይም ጫና ማሳደሩ አልቀረም።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንዳሉት፤ በፓስፖርት አሰጣጥ ሂደት ላይ ሙስናና ብልሹ አሰራር በግልጽ ይታያል።

በመሆኑም ኤጀንሲው በፓስፖረት አሰጣጥና የቁጥጥር ጣቢያዎች ላይ የሚታየውን የተበላሸ አሰራር እንዲቆም ማደረግ አለበት ብለዋል።

በጨረታ ሂደት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ከፓስፖርት አቅራቢው ድርጅት ጋር ያለው ግንኙነትም ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።

የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል፤ የኢትዮጵያ ፓስፖርት ዲዛይን በአቅራቢ ድርጅቱ እጅ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ኦቨር ቱር ከተባለ የፈረንሳይ ፓስፖርት አቅራቢ ድርጅት ጋር ለረጅም ዘመናት ስትሰራ መቆየቷን ጠቁመዋል።

የፈረንሳዩ ፓስፖርት አቅራቢ ድርጅት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በገባው ውል መሰረት የሚጠበቅበትን የፓስፖርት ቁጥር ሲያቀርብ ቆይቷል።

ሆኖም አቅራቢ ድርጅቱ በ2009 እና 2010 ዓ.ም ያቀረበው የፓስፖርት መጠን ከሚጠበቅበት በታች መሆኑ ታውቋል።

በዚህ ላይ እያለ “ኦቨር ቱር” የተባለው ድርጅት የፓስፖርት ህትመት ቴክኖሎጂውን “ኢንዴሚያ” ለተባለ ሌላ ድርጅት በመሸጡና የፓስፖርቱ ዲዛይን በድርጅቱ እጅ በመሆኑ “ኢንዴሚያ” እንዲያቀርብ ተደርጓል ብለዋል።

በ2011 ዓ.ም የነበረው ፓስፖርት ከ200 ሺህ በታች ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የቀረበውን ፓስፖርት በጣም ለሚያስፈልጋቸው አካላት ለመስጠት ተገደናል ብለዋል።

እንደ አቶ ሙጂብ ገለፃ አንዳንዶች ፓስፖርት ለማግኘት ሲሉ በአንድ በኩል የሃሰት ማስረጃ በሌላ በኩል ደግሞ በገንዘብ እየደለሉ ለማውጣት ይጥራሉ።

የፓስፖርት የጨረታ ሂደት ዓለም አቀፍ ሂደትን የተከተለ መሆን ስላለበትና አዲስ ዲዛይን ለማውጣት ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ወደ ጨረታ ከመገባቱ በፊት አሁን ከሚያቀርበው ድርጅት ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥረን ያለንን የፓስፖርት ክምችት መጠን ማብዛት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

ኤጀንሲው አሁን ያለው የፓስፖርት መጠን ውስን መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከድርጅቱ ጋር በመነጋገር እስከ መጭው ታህሳስ ወር 400 ሺህ ተጨማሪ ፓርፖርት እናስገባለን ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ መልካም የሚሰሩትን በማበረታታትና አጥፊዎችን በመቅጣት ሙስናና ብልሹ አሰራር መከላከል አለበት ብለዋል።

በሁሉም የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ፓስፖርት ለማውጣት የሚታየውን ሰልፍ ለመቀነስ ሌሎች አማራጮችን እናያለን ብለዋል አቶ ሙጂብ።

 (ENA)

Report Page