#ETH

#ETH


የሲዳማ ዞን ህዝበ ውስኔ ምርጫ ለማስፈጸም ወደ ቦታው ያቀኑ አስፈጻሚዎች በሐዋሳ እየተንገላቱ መሆኑን ተናገሩ!

(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)

የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን ህዝበ ውሳኔው ደግሞ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።

ህዝበ ውሳኔውን በበላይነት የሚያስፈፅመው የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ6ሺህ የሚልቁ የምርጫ አስፈጻሚዎችምን ትላንት ወደ ሀዋሳ ከተማና የሲዳማ ወረዳዎች ልኳል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም ተመልምለው ወደ ሀዋሳ ከተላኩት የምርጫ አስፈጻሚዎች እንደሰማው ከ400 የሚልቁ አስፈጻሚዎች አሁንም በሀዋሳ ከተማ እንግልት እየደረሰባቸው ነው፡፡

አንድም የሚያናግረን ሰው አጥተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ምላሽ የሚሰጠን እና የምናናግረው አንድም ሰው የለም ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ብንደውል የስራ ሀላፊዎቹ ስልካችን ዘግተዋል ይላሉ፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም በጉዳዩ ዙሪያ የምርጫ ቦርድ የስራ አመራሮች ምላሽ እንዲሰጡበት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም።

የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሌዳሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት በእኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ዝግጅት አድርገናል እንደተባለው የአስጻሚነት ቦታቸውን ያላወቁ ከ400 የሚልቁ ወጣቶችን አግኝተን አናግረናል፡፡

እኛ መመደብ ስለማንችል ለሚመለከተው የምርጫ ቦርድ ነገሩን አሳውቀናል እስከዛው ግን የሀዋሳ ከተማ አስተዳዳርና የሲዳማ ዞን ቁርስ እና ምሳ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሯሯጥን ነው ብለዋል፡፡

ይህ እንዴት ተፈጠረ ለሚለው ግን የስራው ባለቤት እኛ ሳንሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመሆኑ እርሱን አናግሩ ብለዋል አስተዳዳሪው፡፡

በህዝበ ውሳኔው የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞን በሚገኙ 66 ወረዳዎች እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ ነዋሪዎች ለመራጭነት ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚገመት አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡

የመራጮች ምዝገባ በሀዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን ወረዳዎች በሚገኙ 598 ቀበሌዎች በ1ሺህ 692 የምርጫ ጣቢያዎች ይካሄዳል፡፡

(ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8)

ያይኔአበባ ሻምበል

Report Page