#ETH

#ETH


የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የመራጮች ምዝገባ ከሁለት ቀናት በኋላ እንደሚጀመር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፦

ህዳር 10 ፣2012 ለሚካሄደው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጠት የሚፈልጉ ከጥቅምት 26 እስከ ህዳር 6 ፣2012 ባሉት 10 ቀናት መመዝገብ እንደሚኖርባቸው ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በድምጽ ሰጭነት ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችም አስቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት

• በሲዳማ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ውስጥ ነዋሪ የሆነ/የሆነች

• ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ/የሆነች፣

• በምዝገባው ዕለት ዕድሜው 18 አመት እና ከዚያ በላይ የሆነ/የሆነች፣

• በቀበሌው 6 ወር የኖረ/የኖረች ናቸው፡፡

ቦርዱ በድምፅ ሰጪነት ሊመዘገቡ የማይችሉ አካላትንም አሳውቋል፡፡ በዚህም

• ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያልሆነ/ያልሆነች፣

• በምዝገባው ዕለት ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች የሆነ/የሆነች እና በድምፅ መስጫ ጣቢያው ከ6 ወር በታች የኖሩ

• በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል የተረጋገጠበት/የተረጋገጠባት ሰው

• የመምረጥ መብቱ በህግ ወይም አግባብ ባለው ህግ መሰረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበበት/የተገደበባት ሰው ናቸው፡፡

የድምፅ ሰጭዎች ምዝገባ ቦታና የምዝገባ ሁኔታንም ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡

• የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ የሚከናወነው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ እንዲካሄድ በተጠየቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ብቻ ነው፡፡

• ምርጫ አስፈጻሚዎች ቤት ለቤት ምዝገባ አያከናውኑም፡፡

በድምፅ ሰጭዎች ምዝገባ ቦታ መገኘት ያለባቸው አካላትም የህዝበ ውሳኔ አስፈፃሚዎች፣ወኪሎች፣ቅሬታ ለመፍታት ከህዝቡ የተመረጡ ኮሚቴዎች፣እድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ድምፅ ሰጪዎች እና ቦርዱ ፍቃድ የሰጣቸው አካላት ብቻ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡

• የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ በይፋ ባወጣው ቀናት መሰረት ከጥቅምት 26- ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም በ ከጠዋቱ 2፡30-6፡30 ከቀትር በኃላ 7፡30-11፡30 ሰዓት ቅዳሜና እሁድ ጨምሮ ይካሄዳል፡፡

• የምርጫ አስተባባሪዎችም የምዝገባውን ቀን በየአካባቢው በማስታወቂያ በቀላሉ ሊታዩ በሚችሉባቸው ቦታዎች ላይ ይለጥፋሉ፡፡

ለምዝገባ የሚቀርቡ የማንነት ማስረጃዎች

• የህዝበ ውሳኔ ተመዝጋቢው በመደበኛነት ነዋሪ መሆኑን እና ማንነቱን የሚያሳይ ሰነድ በማቅረብ መመዝገብ ይችላል፡፡

• አስፈጻሚዎች የተመዝጋቢውን ነዋሪነት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡

የአመዘጋገብ ሂደት

• የመዝገብ ሹሙ መመዘኛውን የሚያሟላ ሰው በግንባር ቀርቦ ማሰረጃውን ሲያሳይ መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡

• ለምዝገባ የቀረበ ሰው እንደ አመጣጡ ተራውን ጠብቆ ከመዝገብ ሹሞቹ አንደኛው ፊት መቅረብና መዝጋቢዎች የሚጠይቁትን የማንነት ጥያቄ በትክክል መመለስ አለበት፡፡

• ተመዝጋቢውም በመራጮች መዝገቡ ላይ በስሙ ትይዩ ፊርማውን ወይም የጣት አሻራ እንዲያስቀምጥ ይደረጋል፤የመራጮች ካርድም ይሰጠዋል፡፡

• መራጮች በግንባር ቀርበው ካልሆነ በስተቀር በውክልና ሊመዘገቡ አይችሉም፡፡

• እድሜያቸው የገፉ፣ አካል ጉዳተኞች እና ህጻናት ልጆችን ያያዙ ወላጆች ተራ ሳይጠብቁ ለምርጫ ጣቢያው ሀላፊ በማሳወቅ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መመዝገብ አለባቸው፡፡

• ማየት የተሳናቸው እና አቅም የሚያንሳቸው ሰዎች በአካል ተገኝተው በሚመርጡት ሰው በመረዳት መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን፤ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ረዳት ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ፤

• ኢትዮጵያዊ የሆነ፣

• እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነው እና

• ከሁለቱ ወገን በወኪልነት ያልተመደበ ሰው መሆን ይኖርበታል፡፡

ስለድምፅ ሰጪ ምዝገባ መታወቂያ ካርድ

• የድምጽ ሰጭ ምዝገባ መታወቂያ ካርድ የሚሰጠው በህጉ መሠረት ለተመዘገበ ሰው ነው፣

• ድምፅ ሰጪው የተሰጠውን የመራጭነት መታወቂያ ካርድ በጥንቃቄ መያዝ ይገባዋል፡፡

• ሆኖም በተለያዩ አስቸጋሪ ምክንያቶች ካርዱ የጠፋበት ወይም የተበላሸበት መራጭ ከድምጽ መስጫው እለት በፊት ባሉት የሥራ ጊዜያት ወይም በድምፅ መስጫው እለት ለምርጫ ጣቢያው ሊያመለክት ይችላል፡፡ ጥያቄው ከታመነበትም ጉዳዩን በቃለ ጉባዔ በመያዝ በመዝገብ ላይ ስሙን እና አለመምረጡን በማረጋገጥ ድምጽ ሊሰጥ እንደሚችል ሊታወቅ ይገባል፡፡

በምዝገባ ሂደት የተከለከሉ ተግባራት

• በህዝበ ውሳኔ የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ወቅት መመዘኛዎችን የማያሟላ ነገር ግን በመራጭነት ተመዝግቦ የተገኘ፣

• ድምፅ ሰጪው አለማሟላቱን እያወቀ መዝግቦ የተገኘ መዝገብ ሹም፣

• ለድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ ከተወሰነው ቀንና ሰዓት ውጭ ምዝገባ ያከናወነ የመዝገብ ሹም፤

• በአንድ የህዝበ ውሳኔ ጣቢያ ከአንድ ጊዜ በላይ ወይም ከአንድ ምርጫ ጣቢያ በላይ ተመዝግቦ የተገኘ፣

• ከአንድ በላይ የምዝገባ መታወቂያ ካርድ ይዞ የተገኘ ሰው፣ ለመመዝገብ ሲል የሀሰት መግለጫ ወይም ማስረጃ የሰጠ ወይም ያቀረበ፣

• መራጮች እንዳይመዘገቡ ያስፈራራ ወይም የሀሰት መረጃ ወይም ማስረጃ የሰጠ፣

• የመመዝገብ ወይም አቤቱታ የማቅረብ መብትን የከለከለ ወይም የገደበ ወይም ያወከ፣

• የህዝበ ውሳኔ ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ መታወቂያ ካርድን የለወጠ፣ የሰረዘ፣ የደለዘ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበን

መራጭ የሠረዘ ወይም የደለዘ እና በህዝበ ውሳኔ ጣቢያው ኃላፊው ከተመደቡ መዝጋቢዎች ውጪ የመራጮች ምዝገባ በህግ ይጠየቃል፡፡

የምዝገባ ሂደት ላይ ያለ ቅሬታ

• በምዝገባ ሂደቱ ላይ ቅሬታ ያለው ሰው በድምጽ መስጫ ጣቢያው ውስጥ ለሚደራጀው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡

• አቤቱታው እንዳልተፈታለት ያመነ ሰው በዞን ደረጃ ለሚቋቋመው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንዲሁም በማስከተል ለፍርድ ቤት አቤት የማለት መብት እንዳለው ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

(EBC)

Report Page