#ETH

#ETH



በአገሪቷ የሚሰጡ ብሄራዊ ፈተናዎች ላይ ለሚፈጠሩ ችግሮች ተጠያቂ የሆኑ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትምህርት ሚኒስቴር የ2012 በጀት አመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ላይ ከሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ጋር መክሯል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የሚሰጡ ብሄራዊ ፈተናዎች በተደጋጋሚ ችግሮች እየተፈጠሩበት ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን ከ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር ተያይዞ የተማሪዎች ውጤት ላይ ችግሮች መፈጠራቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ይኸውም በተማሪዎች፣ በወላጆችና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት።

ከተፈጠሩት ችግሮች ጋር ተያይዞም በትምህርት ሚኒስቴርና በኤጀንሲው ችግሩ በአስቸኳይ ተጣርቶ እርምጃ መወሰድ ነበረበት ብለዋል።

በተቋማቱ ኃላፊዎች በኩልም ችግሩን ለማድበስበስና ተጠያቂነትን ወደ ሌላ አካል ለማስተላለፍ ከመሞከር ይልቅ ኃላፊነት ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴርና የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ከፈተናው ውጤት ጋር ተያይዞ ዋነኛ ተጠያቂ መሆናቸውንና  የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጃትና አሰራር ለመፍጠር አለመቻላቸውንም ተናግረዋል የምክር ቤቱ አባላት።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ወደ 3 ሚሊየን የሚሆኑ የትምህርት እድል ያላገኙ ህጻናትና ወጣቶች በአገሪቷ እንደሚገኙ የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመላክት አንስተዋል።

ይህ ክፍተት የተፈጠረውም በትምህርት ዘርፍ ባሉ ባለድርሻ አካላት የቅንጅትና የአመራር ክፍተት ሳቢያ በመሆኑ እዚህም ላይ ብዙ መሰራት ይኖርበታል ተብሏል።

ከትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ጋር ተያይዞም ጥልቀት ያላቸው ውይይቶች መደረግ እንደሚኖርባቸውና ከክልሎች ጋር መግባባት ላይ መደረስ እንደሚኖርበትም በቋሚ ኮሚቴው አባላት ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቱ በሰጡት ምላሽ ከ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ጋር ተያየዞ የተፈጠረው ችግር ለማጣራትና ተጠያቂነትን ለማስፈንም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩና በኤጀንሲው በኩልም ተገቢውን ማጣሪያ በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ወደ ትምህርት ገበታ የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር ለማሳደግም ክልሎችንና ወረዳ ድረስ ያሉ አደረጃጃቶችን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተማሪዎች ምዝገባ አነስተኛ በሆነባቸው ክልሎች ላይም የመስክ ምልከታና ልዩ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

ባለፈው ዓመት በአገሪቷ ግጭት በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው መከፈታቸውንና ከትምህርታቸው የተስተጓጎሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታውን በተመለከተም ከክልሎች ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮች መነሻ የመረጃ ክፍተት መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም በስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል ሚኒስትሩ።

(ኢዜአ)

Report Page