#ETH

#ETH


መንግሥት ለመረጃው አዲስ መሆኑንና በጂቡቲ በኩል ለማስመጣት እየሠራሁ ነው ብሏል

በየመን ጂዋዛት በሚባል ማቆያ ጣቢያና በተለያዩ አካባቢዎች ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመታት በእስር መቆየታቸውን የሚናገሩ ከ650 በላይ ኢትዮጵያውያን፣ የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑ ታወቀ፡፡

መንግሥት በበኩሉ ኢትዮጵያ በየመን ኤምባሲ እንደሌላት ጠቁሞ፣ ኢትዮጵያውያን በየመን መኖራቸውንም ሆነ ስለሚደርስባቸው ችግር የሚያውቅበት ምንም ዓይነት መንገድ እንዳልነበረ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያኑ ችግር ላይ መሆናቸውን ከሰማ ጥቂት ቀናት ቢሆንም፣ በጂቡቲ በኩል ለማስመጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ የመን ውስጥ የታሰሩት በሕገወጥ መንገድ በየመን አቋርጠው ሳዑዲ ዓረቢያ ለመግባት ሲሉ፣ የሁቲ አማፅያን በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው ገልጸዋል፡፡ አማፅያኑ በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው፣ ‹‹ወደ አገራችሁ ትመለሳላችሁ፤›› በማለት ‹‹ሳዓዳ›› በሚባል ቦታ አስረው ካቆዩአቸው በኋላ ወደ ሰንዓ እንደወሰዷቸውም አክለዋል፡፡

በሰንዓ ታስረው የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ምግብም ሆነ ሕክምና በበቂ ሁኔታ እንደማያገኙ፣ ብዙዎቹ ለአዕምሮ ጤና መቃወስ መጋለጣቸውንና ከመሀላቸው ጓደኞቻቸውም እንደሞቱ ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) የሚያደርግላቸው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን፣ ምግብም ሆነ ሌሎች ዕርዳታዎችን የሚያቀርቡላቸው ሠራተኞች የመናውያን በመሆናቸው፣ ከወታደሮች ጋር እየተስማሙ ብዙውን ዕርዳታ እንደሚያስቀሩ ተናግረዋል፡፡

ወደ አገራቸው እንዲመልሷቸው ሲጠይቁ አስለቃሽ ጭስ በላያቸው በመወርወር እያሰቃዩዋቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ መረጃው የደረሰው ኢትዮጵያዊ ወይም መንግሥት ካሉበት የሲኦል ኑሮ እንዲያወጣቸው ተማፅነዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ደረሰብን ስለሚሉት ሥቃይና ሞት በሚመለከት ምን እያደረገ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው፣ ‹‹ጉዳዩን የሰማነው ትናንትናና ዛሬ (ጥቅምት 20 እና 21 ቀን 2012 ዓ.ም.) ነው፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በየመን ኤምባሲ የላትም፡፡ ከዚህ ቀደምም በችግር ላይ የነበሩ ሰዎችን ያስወጣነው ጂቡቲ ባለው ኤምባሲ በኩል ነው፡፡ ከየመን ወደ ጂቡቲ እንዲመጡ ተደርጎ ነው የተመለሱት፤›› ብለዋል፡፡

አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲፈጸም በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር መነጋገራቸውን፣ የተወሰኑ ሰዎች ከየመን በመውጣት ኦቦክ በሚባል መጠለያ ጣቢያ (ጂቡቲ) የደረሱ መኖራቸውንና ሌሎቹም በተመሳሳይ እንዲመጡ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

(ሪፖርተር)

Report Page