#Eth

#Eth


የአዳማ ከንቲባ ንግግር የአማርኛ ትርጉም ሲፈተሽ!

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ነው የተባለ እና ሁለት ደቂቃ ከአስራ አምስት ሰከንድ የሚረዝም ንግግር ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በተለይም በፌስቡክ ሲዘዋወር ሰንብቷል። በትንሹ አስራ ስድስት የፌስቡክ ገፆች ላይ የተጫነው ይኸው ንግግር በአፋን ኦሮሞ የተደረገ ሲሆን ወደ አማርኛ የተረጎመው ወገን ማንነት ግን አልተገለጸም። 

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ሰሞኑን በአዳማ ከተማ አቅራቢያ ዶቆኑ በተሰኘ ቦታ ከሐረር እና አካባቢው ተፈናቅለው ለተጠለሉ ሰዎች በኦሮሚኛ ያደረጉት ንግግር ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ተሰራጭተዋል። በማኅበራዊ ድረ ገፆች በተሰራጨው የከንቲባው ንግግር ቄሮ ተብለው ለሚጠሩ የኦሮሞ ወጣቶች የጦር መሳሪያ ለማስታጠቅ ቃል ገብተዋል የሚል መልዕክት ተሰራጭቷል። በእርግጥ አቶ አሰግድ ጌታቸው በንግግራቸው እንዲያ ብለዋል?

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ነው የተባለ እና ሁለት ደቂቃ ከአስራ አምስት ሰከንድ የሚረዝም ንግግር ወደ አማርኛ ተተርጉሞ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በተለይም በፌስቡክ ሲዘዋወር ሰንብቷል። በትንሹ አስራ ስድስት የፌስቡክ ገፆች ላይ የተጫነው ይኸው ንግግር በአፋን ኦሮሞ የተደረገ ሲሆን ወደ አማርኛ የተረጎመው ወገን ማንነት ግን አልተገለጸም። 

በተንቀሳቃሽ ምስሉ ንግግር ሲያደርጉ የሚታዩት ግን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ሳይሆኑ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ አሰግድ ጌታቸው ናቸው። የከንቲባው ንግግር አርብ ጥቅምት 2012 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አስተዳደር ስር በምትገኘው ዶቆኑ የተሰኘች እና ከሐረር የተፈናቀሉ ዜጎች መጠለያ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ወጣቶች ቤተሰቦችን ለማጽናናት ወደ ስፍራው ባመሩበት ወቅት ከነዋሪዎች ጋር ካደረጉት ድንገተኛ ውይይት ላይ የተቀነጨበ ስለመሆኑ ዶይቼ ቬለ አረጋግጧል።

ወደ አማርኛ የተተረጎመ የተባለው የከንቲባውን ንግግር በተጫነበት ኢትዮጵያ ሐገሬ የተባለ የፌስቡክ ገጽ ብቻ ከ24 ሺሕ ጊዜ በላይ ታይቷል። ከ900 ጊዜ በላይ ተጋርቷል። የከንቲባው የአፋን ኦሮሞ ንግግር እና ከንግግሮቻቸው ተቀንጭበው በአማርኛ የተሰራጩት መልዕክክቶች ግን መሰረታዊ ልዩነት አላቸው። በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ነው ተብሎ በተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምስል "በአዳማ ወይም ናዝሬት ያሉትን ቄሮዎች እናንተን ጠመንጃ እናስታጥቃችኋለን" ብለዋል የሚል ይገኝበታል። 

በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በተሰራጨው የአቶ አሰግድ ጌታቸው ንግግር ግን በአማርኛ ከተፃፈው የተለየነው። ከንቲባው “ከታጣቂ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ሃሳብ እኔ ምንም መረጃ አልነበረኝም ፤ በቅርቡ ነው የመጣሁት ፤በቀበሌያችሁ የታጠቀ ሰው ከሌለ ህጋዊ የሆነ ሰው ፣ ስነምግባር ያለው ሰው መርጣችሁ ትሰጡናላችሁ እናስታጥቅላችኋለን» ብለዋል። 

በርካቶች በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በተቀባበሉት ቪዲዮ "ከፋኖ ላይ ግን ጠመንጃ ቀምተን፣ ወደ እስር ቤት እናጉራቸዋልን" ብለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። በማኅበራዊ ድረ-ገፆች በተሰራጨው ቪዲዮ እንዲያ አይነት ንግግር የለም። ከንቲባው በቪዲዮው “እዚህ ወንጀል የሰሩ ሰዎች ሰውንም እንደገደሉ እናውቃለን ፤ ስም ትሰጡናላችሁ መሳሪያ እንዴት እንደተኮሱ እንጠይቃቸዋለን። ህገ ወጥ የታጠቀ ሰው ካለ እያንዳንዷን ጠራርገን እናስገባለን” ሲሉ ይደመጣል። 

አቶ አሰግድ ጌታቸው ተናግረዋቸዋል ተብለው በእነዚሁ ማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በቅብብል ሲታዩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በተለይ ከሀይማኖት ጋር በተገናኘ ተተርጉሞ የቀረበው ሀሳብ “ቄስ ትሆን ጳጳስ ቀጥቅጠን እስር ቤት እናስገባቸዋለን፤ የቤተ-ክርስትያን ደወል ደውለው ህዝቡ እንዲሰበሰብ ያደረጉ ቄሶችን ጠራርገን ወደ እስር ቤት እናስገባቸዋለን” የሚል ይገኝበታል። የከንቲባ አሰግድ ንግግር ቀጥታ ትርጉም ግን ከተባለው የተለየ ነው። የከንቲባው ንግግር “ቄስም ሆነ ጳጳስም ቢሆን አንድ የሃይማኖት ሰው ህገ ወጥ የሆነ ስራ አይሰራም ፤ ሰው አይገድልም ፤ ሰው መግደል ገነት አያስገባም ፤ከእኔ በላይ እናንተ ታውቃላችሁ ፤ ይህን ያደረገ ካለ በዚህ ጉዳይ ላይ እጁ ያለበት ካለ ፣ ያንን የሰበከ ቄስም ፣ ከፓትሪያሪኩ ጋርም ተነጋግረናል እዚህ ብቻ አይደለም በመሃል ከተማ ችግር ሳይኖር ደ,ወል ደውለው ህዝቡ ተነቅሎ እንዲወጣ ሲያደርጉ ነበር እነዚህን ለይተን እየያዝን ነው” የሚል ነው። 

ሌላው ከንቲባው በንግግራቸው “ይህ የኦሮሞ ሀገር ነው ማንም እንደፈለገ መፈንጨት አይችልም” ብለዋል ተብሎ ሲታይ የነበረ ነው። የከንቲባው ንግግር “ከዚህ ውጪ ይህ ሀገር ሀገራችን ነው፤ የኦሮሞ ሀገር ነው፤ ከሀረርጌ ብትመጡም የኦሮሞ ምድር ነው ፤ የትም መሄድ የለባችሁም ፤ ወዴትም መንቀሳቀስ የለባችሁም ፤ ምድራችሁ ነው።”

የአዳማ ከተማ ከንቲባ የሆኑት አቶ አሰግድ ጌታቸው እንዳሉት ችግር ተፈጥሮ በነበረበት ወቅት በአንድ መንደር ተሰብስበው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማረጋጋት ያደረኩት ንግግር ከአውድ ውጭ ተተርጉሞብኛል ብለዋል። አንዳንድ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የአንድን ግለሰብ ፣ ድርጅት ወይም ማህበረሰብ ጉዳይ ቀንጭበው በመውሰድ ሌላ ትርጉም እንዲሰጥ አርትዖት በመስራት ተከታዮቻቸው እንዲመለከቱ አልያም እንዲያጋሯቸው ሲያደርጉ ይታያል። እነዚሁ የሃሰት መረጃዎች ጥላቻ እንዲፈጠር፣ ለሁከትና ብጥብጥ የሚጋብዙ ሁኔታዎች እንዲከሰቱም አይነተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

DW


Report Page