#ETH

#ETH


በሊባኖስ ቤይሩት የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጉዳይ ላይ የቅርብ ክትትል የሚያደርግ ግብረ ኃይል ወደ ስፍራው እንደሚጓዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሳምንቱ በተከናወኑ አበይት ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

በሊባኖስ ቤይሩት ላለፉት ሁለት ሳምንታት አለመረጋጋትና ሠላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በአገሪቷ 400 ሺህ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ የሚኒስቴሩ መረጃ የሚጠቁም ሲሆን ሚኒስቴሩም በተፈረጠው አለመረጋጋት ምክንያት በኢትዮጵዊያን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየተሰራ መሆኑን አመልክቷል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በሊባኖስ የሚገኘው ቆንጽላ ጀኔራል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እየሰራ ነው።

እስካሁን ባለው ሁኔታም በችግሩ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ጠቁመዋል።

በአገሪቷ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሰልፎች ላይ እንዳይሳተፉ መልዕክት መተላለፉን የገለጹት ቃል አቀባዩ ፤ እርዳታ ለሚፈልጉም በስልክ መስመር ጥሪ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸቱን አብራርተዋል።

እንደ አቶ ነብያት ገለጻ፤ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በቅርበት ለመከታተልና ለመገምገም ግብረ ኃይል ወደ ስፍራው ለመጓዝ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

”ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያና ሊባኖስ መንግሥት በስራና በዜጎች መብት ጥበቃ ላይ ያተኮረ ስምምነት ለመፈራረም የረቂቅ ሰነዶች ልውውጥ ተካሂድዋል” ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ስምምነቱ በሕጋዊ መንገድ ስራ ይዘው የሚሄዱበት፣ የተለየ የዜጎች መብት ጥበቃ የስምምነቱ ረቂቅ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በጂቡቲ ታጁራና ኡቦክ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተበባበር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እየታለሉ በጂቡቲ በኩል ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ከሞከሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል ባለፉት ሦስት ወራት 1 ሺህ 221 ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንደተመለሱ ተናግረዋል።

ከሳውዲ አረቢያ በቀይ ባህር በኩል የተጓዙና ካምፕ ውስጥ የነበሩ 400 ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ነገ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱም አክለዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዝም ግብጽና ኢትዮጵያ በሩሲያ ሶቺ ከተማ ያደረጉት ውይይት ስኬታማ መሆኑም አንስተዋል።

ቃል አቀባዩ በፖለቲካ ዲፕሎማሲው ዙሪያ በሰጡት መግለጫም የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት ከሁለት ሳምንት በኋላ ለማካሄድ የታቀደ ቢሆንም የሰላም ስምምነቱ ፈራሚዎች የክልሎች ቁጥርና የወሰን ጉዳይ መቋጫ እንዳላገኘ አመልክተዋል።

‘የአገሪቱን ብሄራዊ ጦር የማደራጀት ስራውም እንዲሁ አልተጠናቀቀም’ በሚል ምክንያት በሽግግሩ መንግሥት ምስረታ ላይ እንደማይሳተፉ እየገለጹ ያሉ አካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በአንጻሩ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኬር የሽግግር መንግስት ምስረታው በታየዘው ቀነ ገደብ እንዲካሄድ አቋም እንዳላቸው የጠቁሙት አቶ ነብያት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያለበትን ሁኔታ ከገመገመ በኋላ ምስረታው መካሄድ እንደሚገባው ያለውን ሀሳብ አቅርቧ ሲሉ አመልክተዋል።

ENA

Report Page