#ETH

#ETH


በደቡብ ክልል ተከስቶ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሃብት እንደወደመበት የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አስታወቀ፡፡

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ኃይለጊዮርጊስ ባለፉት ጊዜያት በክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ መደፍረስ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ጉዳት ደርሶበታል።

በጸጥታ መደፍረስ ችግር ምክንያት ተቋሙ በ12 ዲስትሪክቶችና ጽህፈት ቤቶቹ ላይ ቃጠሎ፣ ዝርፊያና የተለያዩ ጉዳቶች እንደደረሱበትም ገልጸዋል።

ጥሬ ገንዘብ፣ የወደሙ ቋሚ ንብረቶች፣ የጽህፈት ዕቃዎች፣ የተለያዩ ህትመቶችና የሕዳሴ ግድብ ቦንድን ጨምሮ 30 ሚሊዮን 659 ሺህ ብር የሚያወጣ ሃብት መውደሙንም ተናግረዋል፡፡

አቶ አለማየሁ እንዳሉት የታርጫ ዲስትሪክትን ጨምሮ በታርጫና ሳውላ ከተሞች እንዲሁም በማራቃ፣ ደንባ ጎፋ፣ ማልጋ፣ ሸበዲኖና ወንዶገነት የሚገኙ የተቋሙ ጽህፈት ቤቶች ቃጠሎ፣ ዝርፊያና ውድመት የገጠማቸው ናቸው።

ለደረሰው ኪሳራ ምክንያት የሆኑ ግለሰቦች በውስጥም በውጭም እንዳሉ ገልጸው መረጃዎችን በማደረጃት በህግ ለመጠየቅ ቢሞከርም አጥጋቢ ውጤት አለማግኘታቸውን አስረድተዋል።

“ተቋሙ የገንዘብ ብድር ስለሚያቀርብ መረጃ ለማጥፋትና የህዝብን ሃብት ጉዳት ላይ ለመጣል የተደረገ ሴራ ነው” ሲሉም አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ በሚያቀርባቸው ቀላል የብድር አማራጮች ብዙዎች በግለሰብ፣ በቤተሰብና በአካባቢ ደረጃ ከአስከፊ ድህነት እንዲላቀቁ በማድረግ በኩል የጎላ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ማህበረሰቡ ተቋሙን ሊጠብቀው እንደሚገባ አቶ አለማየሁ አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የተቋሙ ቅርንጫፎች አንዱ የሆነው የታርጫ ዲስትሪክት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኬያጅ አቶ ታፈሰ ኦሎሎ ተቋሙ የገንዘብ ብድር በማቅረብ በአካባቢው በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ አለመረጋጋት ጸረ-ህዝብና ልማት አመለካከት ባላቸው ግለሰቦች መሪነት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የጽህፈት ቤቱ ሃብት መውደሙን ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ህዝባዊ ለማስመሰል ጥረት መደረጉ ወንጀለኞችን በአግባቡ ለመያዝና የህግ ሂደቶችን ለመከተል አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም አመልክተዋል።

አቶ ታፈሰ እንዳሉት ክስተቱ የህዝብን ጥቅም አደጋ ላይ የጣለ ተግባር በመሆኑ ከመኮነን ባለፈ የተቋሙን ገጽታ የመገንባት ሥራዎችን እየሰሩ ነው፡

ተቋሙ የህዝብና የመንግስት ሃብት በመሆኑ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን የገለጹት ደግሞ በደቡብ ክልል ምክር ቤት የበጀት፣ ፋይናንስና ኦዲት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስራት አበበ ናቸው።

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ በበኩላቸው ተቋሙ ላይ ጉዳት በማድረስ ተግባር የተሳተፉና በወንጀሉ እጃቸው ያለባቸው ግለሰቦችን ለይቶ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ENA

Report Page