#ETH

#ETH


መንግሥት ለሥራ አጥ ወጣቶች ያቀረበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር አቅርቦት ዘግይቶብናል፦ ወጣቶች

በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ እና የወጣቶችን ሕይወት ለመቀየር በተለያዩ ሥራዎች መሰማራት ለሚፈልጉ ወጣቶች መንግሥት 2 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

በፕሮግራሙ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ያለምንም የዕድሜ ገደብ መሳተፍ ሲችሉ፤ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 34 የሚገኙ ወንድ ወጣቶችም በዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጧል።

በአዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የገበያ እና ቢዝነስ ልማት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ መስፍን ፊጡማ በተለይ ለኢቢሲ እንደገለጹት በአሁኑ ሰዓትም 21 ሺህ አባላት ያሏቸው 7 ሺህ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ ሆነዋል።

መንግሥት ለእኢንተርፕራይዞች እስካሁን ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መስጠቱን ነው የተናገሩት።

ይሁን እንጂ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ የብድር አገልግሎት ለማግኘት አለመቻላቸውን በተለይ አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የሚኖሩ ወጣቶች ለኢቢሲ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ወጣቶቹ እንደሚሉት በአቅራቢያቸው ያለው የአዲስ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ቅርንጫፍ ቢሮ “በጀት የለኝም” የሚል መልስ ሰጥቶ ሸኝቷቸዋል፤ በዚህም ቀድመው ለሱቅ ኪራይ ያወጡትን ገንዘብ እንደከሰሩም ነው የተናገሩት።

ለቅሬታው ምላሽ የሰጡት አቶ መስፍን፣ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በአቃቂ ቃሊቲ ብቻ ሳይሆን እንደ ከተማ ደረጃ ያለ ጥያቄ መሆኑን ተናገረዋል።

የብድር አገልግሎት መዘግየት ችግሩ የተፈጠረው በበጀት አለመኖር ምክንያት ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ችግር እና የፋይናንስ ብልሽት እንዳያጋጥም ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል።

በብድር አገልግሎት ፈላጊዎች በኩል “በጀት አልቋል” የሚል ስጋት መኖሩን የገለፁት ኃላፊው፣ የተመደበው የተዘዋዋሪ በጀት ግን በአሁኑ ሰዓት እንዳላለቀ ተናግረዋል።

የብድር አገልግሎት ለማግኘት የተመዘገበ ሰው ሁሉ በተመዘገበበት ቅደም ተከተል መሠረት አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸው፣ ቅሬታ ያቀረቡ ወጣቶችም በተራቸው መሠረት የሚደርሳቸው በመሆኑ በትዕግሥት እንዲጠብቁም አሳስበዋል።

አገልግሎቱ ፍትሐዊ እንዲሆን በጥንቃቄ መመራት እንዳለበት የገለጹት አቶ መስፍን፣ ምናልባት ከተዘዋዋሪ ፈንዱ የብድር አገልግሎትን ሳያገኙ ረጅም ጊዜ የቆዩ ሰዎች ተቋሙ በሚሰጠው መደበኛ የብድር አገልግሎት ውስጥ ገብተው መጠቀም እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

አሁን የተጀመረው የተዘዋዋሪ ፈንድ አገልግሎት ከተጠናቀቀ በኋላ የብድር እና ቁጠባ ተቋሙ የሚሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

በአንዳንድ ቦታዎች ላይ “ወጣቶች ያለዋስትና የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር አገልግሎት እያገኙ ነው” የሚል ቅሬታ እንዳለ የተጠየቁት አቶ መስፍን፣ ያለዋስትና ምንም ብድር እንደማይሰጥ ተናግረዋል።

እንደዚህ ዓይነት የብድር አገልግሎት የሚሰጠው ሥራ አጥ የሆኑትን እና በቂ ሀብት ያላፈሩ ሰዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት በመሆኑ እነዚህ ሰዎች የቤት ወይም የመኪና ዋስትና እንዲያመጡ አይደረግም ብለዋል።

ስለሆነም በተቋሙ ፖሊሲ ውስጥ ከተቀመጡ የዋስትና አማራጮች መካከል የቡድን ዋስትናን ጥቅም ላይ በማዋል አንዱ ለአንዱ ዋስ ሆኖ የብድር አገልግሎት የሚወስድበት ሂደት እንዳለ ነው የተናገሩት።

ተቋሙ ለለፉት 20 ዓመታት በዚህ ሁኔታ ሲሠራ እንደቆየም ጠቁመዋል።

ETV

Report Page