#ETH

#ETH


የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት!

የሀገሪቱን ሰላም ማስጠበቅ የሁሉም ኢትዮያውያን የጋራ ኃላፊነት መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል። ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የሃይማኖት ተቋማትም ይህን የጋራ ኃላፊነት የመወጣትና በዚህ ረገድ ህዝቡን የመምከር ሀገራዊ ግዴታ አለባቸው ብሏል፡፡ ባለፉት ወራት በቤተ አምልኮዎች እና በመስጅዶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ቢፈፀምም ህብረተሰቡን በማረጋጋት ነገሩን በትእግስት ሲያልፍ መቆየቱን ምክር ቤቱ ገልጿል።

ሰሞኑን የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍም ወደ ብጥብጥና ረብሻ በመለወጡ በርካታ የሰው ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ጠቅሷል፡፡ ግጭቱን የሃይማኖቶች ለማስመሰል በእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀሙና የሃይማኖት አባቶች መገደላቸው ችግሩን እጅግ የከፋ አድርጎታል ብሏል።

ለዚህም መንግስት በአጥፊዎች ላይ የህግ ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን ምክር ቤቱ ጠይቋል፡፡ በግጭቱ ሰበብ በጠፋው የሰው ህይወት እና በወደመው ንብረት እጅግ ማዘኑን ምክር ቤቱ ገልፆ ለተጎጂዎች መፅናናትን ተመኝቷል።

 አገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ የተሳካና ሰላሟ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ በየመስጅዱ ጸሎት እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።

Via ኢቢሲ

@tsegabwolde @tikvahethiopia


ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ፦

የአገራችንን ሠላም ማስጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ፣ የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ የጋራ ኃላፊነቶችን መወጣትና ሕዝቡን በዚህ ረገድ መምከር ሃይማኖታዊ እና አገራዊ ግዴታችን ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ ሂደት አንዳንድ ችግሮች እየገጠሙ መሆኑ ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ በአንዳንድ የአገራችን ዞኖችና ወረዳዎች በተከሰተው ችግር ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት መከተሉ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እየገለጸ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል።

ይሁን እንጂ ባለፉት ወራቶች በቤተ-አምልኮዎች እና በተለይም በመስጊዶች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ኅብረተሰቡን በማረጋጋት በትዕግስት ይዞ ቆይቷል። ለአብነት ያክልም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች መስጊዶችን የማፍረስ ዘመቻ በተደጋጋሚ ተከስቷል። በአማራ ክልል በጎንደር ሥላሴ ወረዳ ወፍጠጌ ቀበሌ ማኅበር ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ ከ40 በላይ አባወራዎች ከሚኖሩበት ቦታ በኃይል ተፈናቅለዋል። በምሥራቅ ጎጃም በቢቸና ከተማ በሚገኝ መስጊድ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሞ አማኞች ላይ የሕይወት መጥፋት አደጋ ተከስቷል። በእስቴ 3 መስጊዶች ተቃጥለዋል። በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 ጋጃ መስክ አካበቢ የሚገኘው ሸዋ በር መስጊድ ፈርሷል። በቅርቡ በአዳማ ከተማ ልዩ ስሙ ጎሮ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ መስጊድ እና ቁርኣን ተቃጥሏል። የሰው ሕይወትም ጠፍቷል። እንዲሁም ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረው ሠላማዊ ሠልፍ ቅርጹን በመለወጥ ወደ ብጥብጥ እና ረብሻ በመለወጡ ንብረቶች፣ እንዲሁም የሰው ሕይወት ያጠፋ ሲሆን፣ ግጭቱን የሃይማኖት ለማስመሰል የእምነት ተቋማትም ሲወድሙ የእምነቱ አባቶች እና ደረሶች በድብደባ መገደላቸው (ጉዳዩን) እጅግ የከፋ አድርጎታል።

በቤተ-አምልኮዎች እና መስጊዶች፣ እንዲሁም በሃይማኖቱ ተማሪዎች እና ዑለማዎች ላይ ጥቃት እና ኢ-ሰብዓዊ ግድያ መፈጸሙ አሳሳቢ ስለሆነ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ የማነሣሣት ተግባርን የማይቀበለው እና መስተካከል ያለበት መሆኑን እየገለጽን መንግሥትም በአጥፊዎች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ማስፈን እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን። ይህንን በተመለከተ የኢትዮጵያም ሕዝብ በሃይማኖቱ ሳይከፋፈል፣ መንግሥትም ሕዝብን በማወያየት የአገርን ሠላም በማስጠበቅ ረገድ የወደፊቱን አቅጣጫ ወጣቱን በማስተማርና ወደልማት እንዲያተኩር (በማረድግ) ከፍተኛ ሚናውን እንዲወጣ አክብረን እየጠየቅን፤

በመጨረሻም መላው የአገራችን ሙስሊም ማኅበረሰብ አገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ የተሳካ እና ሠላሟ የተጠበቀ እንዲሆን በየመስጊዶቻችን ዱዓ፣ ቁኑት፣ እንዲሁም ለምስኪኖች ሶደቃ በማውጣት አላህ ከዚህ የሠላም መታጣት ወደ ሠላም እንዲመልሰን በጠቅላይ ምክር ቤቱ ስም እንጠይቃለን!

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት

(Ethiopian Islamic Affairs Supreme Council)

Report Page