#ETH

#ETH


በብሔራዊ ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ በአምስት ቢሊዮን ብር ወጪ የተሠራው አንድነት ፓርክ ተመርቆ ለሕዝብ ክፍት ከሆነበት ከመስከረም 29/ 2012 ጀምሮ ከ 15 ሺሕ በላይ በሚሆኑ ጎብኚዎች ተጎብኝቶ ከኹለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ።

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ታምራት ኃይሉ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከፓርኩ የሚገኘው ገቢ ፓርኩን ለማስፋፋት እና ለመጠበቅ እንዲሁም ለማሻሻል ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸው አረጋዊያን፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ለሀገር በጎ ውለታ የዋሉ ዜጎች ታዳጊ ህፃናት እና የጎዳና ልጆች ፓርኩን በነፃ እንዲጎበኙ መደረጉንም ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ፓርኩን ለመጎብኘት ለሚመጡ ጎብኚዎች ኹለት አይነት የመግቢያ ቲኬቶች ያሉ ሲሆን፣ በመደበኛ መግቢያዎች ኹለት መቶ ብር እንዲሁም የክብር ቲኬት አንድ ሺሕ ብር ይሸጣሉ። ከዚህ በተጨማሪም ፓርኩን የሚጎበኙ የውጪ ሀገራት ዜጎች ከሠላሳ እስከ ሃምሳ የአሜሪካን ዶላር ይከፍላሉ። በዚህም መሰረት አጠቃላይ የጎበኘውን ሰው በመደበኛ ዋጋው ቢገባ ሦስት ሚሊዮን ብር ገደማ ቢጠጋም በነፃ የገበው ጎብኚ ቁጥር ባለመገለፁ ግን ትክክለኛ ዋጋውን ለማወቅ አልተቻለም።

ፓርኩን ለማስፋፋት እና ያልተጠናቀቁ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በርካታ ገንዘብ የሚያስፈልግ በመሆኑ ሁሉንም ሰው በነፃ ለማስጎብኘት እንዳልተቻለ የገለፁት ሥራ አስኪያጁ፣ እስከ አሁን ከፓርኩ የተገኘውን የተጠቃለለ ገቢ ማወቅ አልቻልንም ብለዋል።

አክለውም በአንድ ጊዜ ከፍለው መመልከት ያልቻሉ ግለሰቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሚሰሩባቸው ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ክፍያውን ከደሞዛቸው ላይ በወራት ከፋፍለው መክፈል እንዲችሉ በማድረግ ለማስተናገድ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በፓርኩ ከተሠሩ መስህቦች መካከል የእንስሳት ማቆያና አኳሪየም (የውሃ አካል) አንደኛው ነው። በዚህም ውስጥ የጥቁር አንበሳ መኖሪያ፣ የዝንጀሮ መጠለያ፣ የአሳ ማርቢያ (አኳሪየም) ጨምሮ የ46 ዓይነት ዝርያ ያላቸው ከ300 በላይ ለሚሆኑ እንስሳት መጠለያ የሚሆን ስፍራ፤ እንዲሁም ለእንስሳቱ ምግብ የሚዘጋጅበት እና ሕክምና የሚሰጥበት ቦታ ተካትቶበታል። በመጪው ጥር ወር 312 እንስሳትን የሚይዘው የአንድነት የእንስሳት ማሳያ ተጠናቆ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ታምራት ኃይሉ ገልፀዋል።

በፓርኩ ምረቃ ላይ ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር)፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እና የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ተወካዮች እና አምባሳደሮች መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

ጎብኚዎች ከጉብኝቱ በኋላ የተሰማቸውን ስሜት እና መሻሻል ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሀሳባቸውን የሚያስቀምጡባቸው 6 መዝገቦች በማዘጋጀት ፓርኩን ለጉብኝት ምቹ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ

Report Page