#ETH

#ETH


#ETHIOPIA

በኦሮሚያ ክልል ከተሞች እና በሌሎችም አካባቢዎች ከሰሞኑ የተከሰተውን ሁከትና ግርግር ለማረጋጋት እየሠሩ መሆኑን የደቡብ እና የምሥራቅ ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዛዦች አስታውቀዋል፡፡

በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ሙዘይ መኮነን እንደተናገሩት በባሌ ሮቤ፣ ዶዶላ፣ አዳማ እና ሌሎችም አካባቢዎች ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በቅንጅት እየሠሩ በመሆናቸው አንጻራዊ ሠላም እየታዬ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ከጥቅምት 16/2012 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ ግጭት እንዳልተከሰተም ነው ጄኔራል ሙዘይ ያስረዱት፡፡

ሠራዊቱ እያደረገ ባለው ጥረትም በዶዶላ ከተማ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ያሉትን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረሰብ ክፍሎች ሕጋዊ ከለላ እንዲገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ይህንኑ ሐሳብ በችግሩ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችም ለአብመድ አረጋግጠዋል፡፡ ስጋት ይታይባቸዋል በሚባሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት እንዳይከሰትም የቅድመ መከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ጄኔራሉ፡፡

የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዘውዱ በላይ ደግሞ በሀረር፣ ድሬዳዋ እና አሰበ ተፈሪ ከተሞች ኅብረተሰቡን እያረጋጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች እየታዩ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችንም ከኅብረተሰቡ ጋር በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው›› ብለዋል ጄኔራል ዘውዱ፡፡ እየታዬ ያለው አንፃራዊ ሠላም እንዲደናቀፍ የሚሠሩ ግለሰቦች እንዳሉ ማረጋገጣቸውንም ለአብመድ ጠቁመዋል፡፡

ግለሰቦቹ ሠራዊቱን ከሕዝቡ ለመነጠል እየተጠቀሙበት የሚገኘውን አደናጋሪ ሐሳብ ኅብረተሰቡ ውድቅ በማድረግ ከሠራዊቱ ጎን መቆም እንደሚጠበቅበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

Via አብመድ


Report Page