#ETH

#ETH


ለ40 ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና የገበያ ልማት ማዕከል፣ ዕድሳት ሊካሄድበት እንደታሰበና ለዕድሳቱም ከ15 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው አስታወቀ፡፡ ኮሜርሺያል ኖሚኒስ በ60 ሚሊዮን የገና ዓውደ ርዕይን በማዘጋጀት የመጀመሪያው መንግሥታዊ ተቋም ሊሆን ነው፡፡

የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት አድማሱ እንዳስታወቁት፣ የበርካታ ንግድ ኩነቶች መናኸሪያ የሆነው ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደ አዲስ ታድሶና ተስፋፍቶ ዘመናዊ የንግድ ዓውደ ርዕዮችን ለማስተናገድ የሚያስችለውን አቅም ለመፍጠር ታስቦ ዕድሳት እንዲካሄድለት ታቅዷል፡፡ ይህን ለማከናወንም የ15 ቢሊዮን ብር በጀት ፈርሶ እንዲሠራ የሚያስችል አቅንቅስቃሴ እንደሚጀመር አቶ ታምራት አስታውቀዋል፡፡ በተለይም የዱባይ ባለሀብቶች ለዚህ ግንባታ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር የሚተዳደረው ኮሜርሺያል ኖሚኒስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለመጪው የገና በዓል የንግድ ዓውደ ርዕይ 60 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታወቋል፡፡

የንግድ ዓውደ ርዕዩን ለማዘጋጀት ለኤግዚቢሽን ማዕከል የጨረታ ዋጋ ከ38.4 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈሉን ያስታወቁት የኮሜርሺያል ኖሚኒስ ተጠሪ አቶ ገብረሕይወት ጌታሁን፣ ለንግድ ዓውደ ርዕዩ ዝግጅት 20 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለተጨማሪ ቀናት ክፍያ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ በመክፈል በጠቅላላው ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የዘንድሮውን የገና የንግድ ትርዒትና ባዛር ‹‹ሰላም የገና ባዛርና ፌስቲቫል›› በሚል ርዕስ ልዩ ዝግጅት ማሰናዳቱን አስታውቀዋል፡፡ ዝግጀቱን በተባባሪነት ሲሳይ አድርሴ የተሰኘ የግል የፕሮሞሽን ኩባንያ እንደሚያሰናዳው ሲገለጽ፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች እንደሚታሙበት ይጠበቃል፡፡

ኮሜርሺያል ኖሚኒስ በ1958 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በቀድሞው ሞርጌጅ ባንክ የጋራ ባለቤትነት የተመሠረተ ኩባንያ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በንግድ ባንክ ሥር የሚተዳደር፣ በሰው ኃይል አቅርቦትና ቅጥር፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶች ሕንፃና ቤቶች የውክልና አስተዳደር፣ በተለያዩ ትዕይንቶች ዝግጅት፣ በደመወዝ ክፍያ፣ በባንክ ወኪልነት፣ በሐዋላ አገልግሎት፣ በአክሲዮን አሻሻጭነት፣ በፕሮፊደንት ፈንድና በመሳሰሉት አገልግሎቶች የተሰማራ መንግሥታዊ ተቋም  ነው፡፡

REPORTER

Report Page