#ETH

#ETH


አዳማ

ዶ/ር ደሳለኝ ፍቃዱ በአዳማ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ናቸው። ከረቡዕ እስከ ዛሬ (ዓርብ) ድረስ ወደ አዳማ ሆስፒታል ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ ሰዎች እና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቶ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር በጠቅላላው 16 መሆኑን ያስረዳሉ።

ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት ረቡዕ ዕለት የ3 ሰዎች አስክሬን ወደ ሆስፒታል መጥቷል። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ አፍሪካ ዱቄት ፋብሪካ ዘበኛ ጥይት ተኩሶ የገደላቸው ሰዎች ይገኙበታል።

የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ራውዳ ሁሴን የዱቄት ፋብሪካው ጥበቃ ጥይት ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ ሰልፈኞ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖች ማቃጠላቸውን ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር ደሳለኝ ትናንት ሐሙስ ሆስፒታሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ተጎጂዎችን ያስተናገደበት ቀን እንደሆነ ያስረዳሉ። "ትናንት ጉዳት ደርሶባቸው የመጡት ሰዎች ቁጥር ከ100 በላይ ይሆናል" ያሉ ሲሆን የጉዳቱ መጠን ከከባድ እስከ ቀላል የሚባል እንደሆነ ያሰረዳሉ።

"በዱላ የተደበደቡ፣ በስለት ጭንቅላታቸው ላይ የተመቱ፣ በጥይት የተመቱ ሰዎችም አሉበት" የሚሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ትናንት ብቻ ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው የመጣ እና በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው የያለፈ ሰዎች ቁጥር 12 ነው ይላሉ።

ረቡዕ ዕለት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከፍተኛ የህክምና ክትትል ክፍል (አይሲዩ) ውስጥ የነበረ ወጣት ዛሬ ጠዋት ህይወቱ አልፏል ብለዋል።

"አሁንም በሆስፒታሉ በአደጋኛ የጤና ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አሉ። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል። አይኑ የጠፋ፣ አጥንቱ የተሰበረ ብዙ ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ እንደሚሉት በከተማው ውስጥ ያለው ግጭት ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ዘልቆ ስለመግባቱም ይናገራሉ። "ወንድሙ የሞተበት አንድ ልጅ አስክሬን ክፍል አቅራቢያ አምርሮ እያለቀሰ ሳለ፤ የተደራጁ ሰዎች የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሲያለቅ የነበረውን ልጅ ላይ ጉዳት አድረሰዋል" ይላሉ።

ይህ ወጣት የቀዶ ህክምና ከተደረገለት በኋላ የጤናው ሁኔታ መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ የሆስፒታሉ ባልደረቦች ከታካሚ ብዛት እያጋጠማቸው ካለው የሥራ ጫና በተጨማሪ በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት መኖሩን ጠቁመው አልፈዋል።

በአዳማ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ ያለ ቢመስልም በግጭት ሳቢያ ጉዳት አጋጥሟቸው ወደ ሆስፒታል የመጡ ሰዎች ስለመኖራቸው ዶ/ር ደሳለኝ ተናግረዋል።

Via BBC

Report Page