TIKVAH ETHIOPIA

TIKVAH ETHIOPIA

TIKVAH ETHIOPIA

ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ከምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት አንጻር!

በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እያከናወናቸው ካሉ ዝግጅቶች መካከል አንዱ የምርጫ ቁሳቁሶችን ማሟላትና ደኅነቱን የጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡ ለመሆኑ በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በዚህ ዙሪያ ምን ልዩ የሆነ ነገር ልንመለከት እንችላለን?

በመራጮች ምዝገባ ወቅት

የመራጮች መዝገብ ከዚህ ቀደም ካለው በተሻለ የደኅንነት መጠበቂያዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡ በዚህም እያንዳንዱ መራጭ የራሱ መለያ ቁጥር ይኖረዋል፣ መራጮች ከሚወስዱት ካርድ በተጨማሪ በመዝገቡ ቀሪ ይኖራል እንዲሁም በቀላሉ ተመሳስሎ እንዳይሰራ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡

ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኀላ መከፈቱ በሚያሳውቅ ቦርሳ ወኪሎችና ታዞቢዎች በተገኙበት ታሽጎ ዝውውር ይደረጋል፡፡ ይህም በልዩ መለያ ቁጥር በሚታሸጉ ሶጥኖች ውስጥ ደኅንነቱ እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ በሚያጠራጥሩ ሳጥኖች ላይ ምርመራ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በድምጽ መስጫ ወቅት

እያንዳንዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት ለጊዜው ያልተገለጹ የደኅንነት መጠበቂያ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ልዩና ሚስጢራዊ ማህተምም ይደረግባቸዋል፣ ቆጠራ የሚደረግባቸውም እነዚሁ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ብቻ ይሆናል፡፡ 

በግልጽ የሚያሳይ የድምጽ መስጫ ሳጥን ሌላው ከዚህ ቀደም የነበረውን ኮሮጆ የተካ ነው፡፡ ሳጥኑ ድምጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት ባዶ መሆኑን በቀላሉ ለማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ሳጥን ልዩ መለያ ቁጥር ያለው ሲሆን ሲዘጉና ሲከፈቱ የማሸጊያ ቁጥራቸው ይመዘገባል፡፡ አንድ ሳጥን ከ800 -1500 ድምጾችን የመያዝ አቅም አለው፡፡ 

ከዚህ ቀደም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለክልል ምክር ቤት የሚሰጡ ድምጾች በአንድ ኮሮጆ ተሰብስበው በቆጠራ ወቅት የሚለዩ ሲሆን በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ግን በተለያዩ ሳጥኖች ድምጹ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሳጥኖቹም በቀለም ይለያያሉ፡፡

የሚስጥር ድምጽ መስጫ መከለያዎች ከዚህ ቀደም በመጋረጃ እንዲሁም በተለያዩ ነገሮች በመከለል የሚከናወን የነበረ ሲሆን በዘንድሮ ምርጫ ግን በቀላሉ የሚገጣጠም በምሥጢር ድምጽ መስጠት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ቁሳቁስ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በሚደርስ መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡

በምርጫ ጣቢያዎች የሚሰቀሉ ማሳወቂያዎች፣ ጠቋሚዎች፣ ልዩ ልዩ ምልክቶች ከዚህ ቀደም ወረቀት በመሆናቸው በቀላሉ ጉዳት ሲደርስባቸው ቆይቷል ይህንን ለመቅረፍም ስቲከሮችንና የጨርቅ ህትመቶች ተዘጋጅተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በመራጮች ምዝገባ ወቅት እንዲሁም በድምጽ መስጫ ወቅት የሚያገለግሉ የተለያዩ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ ባትሪዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች መለያ ልብሶችና መታወቂያዎች ምርጫ ቦርድ ግዢ ፈጽሞባቸው ባሉት የተለያዩ ማዕከላት በልዩ ጥበቃ ስር ያሉ ናቸው፡፡

Report Page