#ETH

#ETH


በአክቲቪስት ጀዋር ሞሐመድ መኖሪያ ቤት አጋጠመ የተባለውን ክስተት ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ከትናንት ጀምሮ ሲካሄዱ ከቆዩት የተቃውሞ ሰልፎች በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 27 ደርሷል።

ዛሬ የተቃውሞ ሰልፍ ተደርጎባቸው ሰው ከሞተባቸው አከባቢዎች መካከል አምቦ፣ ድሬ ዳዋ እና ዶዶላ ይገኙበታል።

አምቦ

ትናንት በአምቦ ከተማ ከተገደሉት ሶስት ሰዎች በተጨማሪ ዛሬ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። ዛሬ በጥይት ከተገደሉት መካከል የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ሞሮዳ ሞሳ የሚባሉ ይገኙበታል በማለት ነዋሪዎች ተናግረዋል። አቶ ሞረዳ ልጃቸውን ፍለጋ በወጡበት ከጸጥታ አስከባሪ ኃይል በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸውን የከተማው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአምቦ ዛሬ ከተገደሉት ሁለት ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎቸ በጥይት ተመትተዋል።

የአምቦ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ደበበ ፈጠነ፤ "ዛሬ 14 ሰዎች በጥይት ተመተው እኛ ጋር መጥተዋል። ሁለቱ ህይታቸው አልፏል። 9 ሰዎች ደግሞ ተኝተው እየታከሙ ሲሆን የተቀሩት ቀላል ህክምና ተደርጎላቸው ወደየቤታቸው ተመልሰዋል" በማለት ያስረዳሉ።

አቶ ደበበ ወደ ሆስፒታላቸው የመጡት ሰዎች በሙሉ ወንዶች መሆናቸውን እና ዕድሜያቸውም ከ17-80 እንደሚገመት ተናግረዋል።

በዚህም በአምቦ ትናንት 3፤ ዛሬ 2 በድምሩ የሟቾች ቁጥር 5 ደርሷል።

ምስራቅ ሃረርጌ

በሁለቱ ቀናት በምስራቅ ሃረርጌ በተካሄዱት ሰልፎች የሟቾች ቁጥር 6 መድረሱን ሰምተናል።

በዞኑ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ አየለ ዴሬሳ በምስራቅ ሃረርጌ በሚገኙ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው እንደነበረ ተናግረው፤ በሁለት ከተሞች በተፈጠረው ግጭት የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በተቀሩት ከተሞች ግን የተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች በሰላም መጠናቀቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አየለ፤ ትናንት 5ቱ ሰዎች የተገደሉት ጉሮ ጉቱ በምትባል ከተማ ወደ ብሄር በተቀየር ግጭት ስለመሆኑ ይናገራሉ። "አንድ ባለሃብት የደህንነት ስጋት ተሰምቶት ሁለት ሰዎችን በጥይት መትቶ ገደለ። ከዚያም በቂም በቀል ግለሰቡ እና ሁለት የቤተሰብ አባላቱ ተገደሉ" ሲሉ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

የአወዳይ ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ከመከላከያ ሠራዊት በተተኮሰ ጥይት ስለመገደሉ የአወዳይ ከተማ ከንቲባ ጃፋር ሙሐመድ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዶዶላ

በምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ከተማ ትናንት እና ዛሬ በነበሩ ግጭቶች በጠቅላላው 6 ሰዎች መገደላቸውን ታውቋል።

ዛሬ በነበረ ግጭት 4 ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ ቢዮ ተናግረዋል።

ትናንት ደግሞ ሁለት ሰዎች ተገድለው ነበር።

በአካባቢው ከጠዋት ጀምሮ ሠልፍ እንደነበር የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ከሰዓት በኋላ ግን ይህ ሠልፍ መልኩን መቀየሩን ይናገራሉ።

ሁኔታው አስፈሪ ስለነበር ለሕይወታቸው የሰጉ ሰዎች በአካባቢው በምትገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው አንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሐረር

በሐረር ከተማ ትናንት 3 ሰዎች መገደላቸውን ከነዋሪዎች ሰምተናል።

ድሬ ደዋ

በድሬ ደዋ ከተማም ትናንት 1 ሰው የተገደለ ሲሆን ዛሬ ደግሞ 4 ሰዎች ተገድለዋል።

የድል ጮራ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አብዱራሃማን አቡበከር ዛሬ ሰባት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታላቸው እንደመጡ ለቢቢሲ ያስረዳሉ። ለህክምና ከመጡት ሰዎች መካከል 4ቱ ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል። ዶ/ር አብዱራሃማን "ሰዎቹ በጥይት እና በሌላ ነገር ነው ጉዳት ደርሶባቸው የመጡት" ሲሉ ተናግረዋል።

አዳማ

ትናንት በአዳማ ከተማ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደው ነበር። ሰልፎቹ ባህርያቸውን በመቀየር በሁለት ጎራ በተከፈሉ ሰዎች መካከል ግጭት ተከስቶ በሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ለጀዋር መሐመድ ድጋፍ ለማሳየት በወጡ ወጣቶች እና እነሱን በሚቃወሙ ቡድኖች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ በሥፍራው የነበረው ሪፖርተራችን ዘግቧል።

የአዳማ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ራውዳ ሁሴን የአንድ የዱቄት ፋብሪካ ጥበቃ ተኩሶ ሁለት ሰዎችን መግደሉን እና በዚህ የተበሳጩ ሰልፈኞ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ 15 መኪኖችን ማቃጠላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

BBC

Report Page