#ETH

#ETH


በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው የባሌ ሮቤ ከተማ ለጀዋር መሐመድ ድጋፍ ከተደረገ ሰልፍ በኋላ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። የባሌ ሮቤ ነዋሪዎች የሐይማኖት መልክ ይዟል ባሉት ግጭት ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች እና ሻይ ቤቶች መቃጠላቸውን የዐይን እማኞች ለጀርመን ራድዮ ተናግረዋል።

የጀርመን ሬድዮ ያነጋገራቸው ሶስት የከተማዋ ነዋሪዎች ከትናንት አመሻሽ ጀምሮ ባሌ ሮቤን ከሌሎች አካባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች፣ የግብይት መደብሮች፣ የመንግሥት እና ማኅበራዊ ተቋማት መዘጋታቸውን አስረድተዋል። ጀዋር መሐመድ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ካሰራጨው መልዕክት በኋላ ትናንት ጠዋት በአብዛኛው ወጣቶች የተሳተፉበት ሰልፍ መካሔዱን የገለጹት ነዋሪዎች በሒደት መልኩን እየቀየረ ወደ ግጭት እና ጥቃት መቀየሩን ተናግረዋል።

«ትናንትና ቄሮ በሚለው ስም የተደራጁ የባሌ ወጣቶች ተነስተው ባንድነት ከተማው ውስጥ እየዞሩ ነበር» ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የባሌ ሮቤ ነዋሪ እማኝታቸውን ሰጥተዋል። ወጣቶቹ «ጀዋር ነው የሚመራን፤ በጀዋር ሥር ነው የምንኖረው፤ ጀዋር ማለት የቄሮ አባት ነው የሚሉ መፈክሮች ያሰሙ ነበር» ብለዋል።

በባሌ ሮቤ የሚገኝ አንድ ቤተ-ክርስቲያን ለማቃጠል ጥረት ተደርጎ እንደነበር የሚጠቅሱት የከተማዋ ነዋሪ ጉዳዩን ወደ ሃይማኖት ግጭት ለመውሰድ እየተደረጉ ስላሉ እርምጃዎች አብራርተዋል። በቤተክርስቲያን ተሰቅሎ የነበረን ባንዲራ ወጣቶቹ አውርደው ማቃጠላቸውን እና ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን ላይ ጥቃት እያደረሱ እንደሚገኙ ተናግረዋል። «የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ንብረት የሆኑ መጠጥ ቤቶች ይሔዱና ያፈርሳሉ። እቃቸውን ውጪ አውጥተው ማንደድ፤ የእሳት አደጋ ማድረስ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ላይ ነው ያሉት» ሲሉ የወጣቶቹን እርምጃዎች ዘርዝረዋል።

አንድ ሌላ የባሌ ሮቤ ነዋሪ በበኩላቸው ሆቴሎችን ኢላማ ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል። ዘርፌ ግርማዬ፣ ባላገሩ እና መስቀል የሚባሉ ሆቴሎች መውደማቸውን የሚናገሩት እኚሁ ነዋሪ በሐረር ሆቴል ላይም ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል። የሮቤው ነዋሪ እንደሚሉት ጥቃት የደረሰባቸው ግለሰቦች የበቀል እርምጃ ሲወስዱ ተመልክተዋል። ከዚህው ጋር በተያያዘ ንብረትነቱ የሙስሊሞች የሆነ «ዌልመል» የተባለ ካፌ ትላንት ምሽት መውደሙን ጠቁመዋል።

የዐይን እማኙ ቢያንስ አምስት ሰዎች ተገድለዋል የሚል ወሬ በከተማዋ መሰማቱን ቢናገሩም ዶይቼ ቬለ ጉዳዩን ከገለልተኛ ወገን ማረጋጥ አልቻለም። «ጠዋት ሰው በጦር መሳሪያ ተመትቶ በቃሬዛ ይዘዋቸው ሲሔዱ አይቻለሁ። በከተማው ጥቃት ሲደርስ ታያለህ» የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ ሁከቱን ወደ ሃይማኖት ግጭት የመቀየር አዝማሚያ እንዳለ ገልጸዋል። «በጣም የሚያሳዝነው ነገር መከላከያ፤ የከተማ ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ያንን ነገር ለማርገብ ምንም አይነት እርምጃ እየወሰዱ አይደለም» ሲሉ በጸጥታ ኃይሎች በኩል የተመለከቱትን ቸልተኝነት ተችተዋል።

DW

Report Page