#ETH

#ETH


በባሌ ዶዶላ ዛሬ በነበረ ግጭት አራት ሰዎች ሞተው ወደ ዶዶላ አጠቃላይ ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቶላ ቢዮ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ትናንት በአካባቢው ከጠዋት ጀምሮ ሠልፍ እንደነበር የተናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ከሰዓት በኋላ ግን ይህ ሠልፍ መልኩን መቀየሩን ይናገራሉ።

በአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደገለፁት የዛሬው ግጭት ሊቀሰቀስ የቻለው "ከሁለት ወር በፊት አንድ ወጣት መሳሪያ በመተኮሱ ለእርሱ በቀል ነው" ሲሉ ይናገራሉ።

በወቅቱ ምንም አይነት ጉዳት ባይደርስም ትናንት ሰልፉን ተከትሎ ግን ግጭት ተከስቶ ሰዎች መጎዳታቸውን፣ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ ሱቆች መዘረፋቸውን ማየቱን ይናገራል።

ሜዲካል ዳይሬክተሩ ትናንት ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መምጣታቸውንና ሕይወታቸው ማለፉን ገልፀው፤ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሦስት ሰዎች ደግሞ ምሽቱን ወደ ሻሸመኔና ሀዋሳ ለህክምና መላካቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ ማለዳ በአካባቢው ግጭት መቀስቀሱንም አረጋግጠው አራት ሰዎች በዱላ ተመትተው ወደ ሆስፒታል እንደመጡና ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።

በዶዶላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ እንደሚናገሩት ግጭቱ የተከሰተው 02 ቀጠና አምስት በመባል በሚታወቀው ስፍራ ሲሆን ስድስት ቤቶች መቃጠላቸውንና ከብቶች መዘረፋቸውን እንዲሁም የንግድ ሱቆች መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ይናገራሉ።

ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን የሚናገሩት ነዋሪው የዛሬው ግጭት ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ሳይሆን እርስ በእርስ የደረሰ መሆኑን ይናገራሉ።

በአካባቢው ያለው ችግር ከፖሊስ ቁጥጥር በላይ ነው የሚሉት ግለሰቡ መከላከያ ገብቶ ሁኔታዎችን ማረጋጋቱን ይናገራሉ።

ሁኔታው አስፈሪ ስለነበር ለሕይወታቸው የሰጉ ሰዎች በአካባቢው በምትገኘው ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው አንደሚገኙ ተናግረዋል።

"እነዚህ ወደ ሆስፒታላችን የመጡ ናቸው" የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ሌሎች የሞቱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ወሬ ከአካባቢው ማህበረሰብ መስማታቸውን ይገልጻሉ።

ዛሬም ተጎድተው ወደ ሆስፒታላቸው ከመጡ መካከል አንድ ግለሰብ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሀዋሳ መላኩን ዶ/ር ቶላ ገልፀው በአሁኑ ሰዓት ወደ ከተማዋ የመከላከያ ሠራዊት መግባቱን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው የአካባቢዎች የመከላከያ ሠራዊት ወደ በስፍራው መግባቱንና የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡን እያረጋጋ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ከጃዋር መሐመድ ጥበቃዎች መነሳት ጋር በተያያዘ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ትናንት በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተካሄዱ ሰልፎችን ተከትሎ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።

BBC

Report Page