#ETH

#ETH


የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፦

ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በዚሁ ወቅት የትምክህት ሐይሎች በአመለካከትና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ጉልበት ፈጥረው አገር የሚያምሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በብዙ የአገራችን አከባቢዎች የሰላም እጦት እየተስፋፋ፣ በዚሁም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግስት የማይቆጣጠራቸው አከባቢዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ። ለመብቱና ለማንነቱ ለታገለ ህዝብ በርካታ ግፍና በደል የሚፈፀምበት፣ ዜጎች በእርጋታ የማይኖሩበት፣ በማንነታቸው ምክንያት በዜጎች ላይ ግፍ የሚፈፀምበት፣ ለህይወታቸውና ንብረታቸው ዋስትና ያጡበት፣ በዚች አገር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ህውከትና መፈናቀል የተበራከተበት፣ መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየተቸገረ የመጣበት፣ ከዚህ አልፎም የአገሪቱ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች እና የአማራ ክልል አመራሮች እስከመግደል ተግባር የተፈፀመበት፣ ሌላ ቀርቶ የነዚህ ምርጥ ጀነራሎችና መሪዎች ግድያ እንኳን በአግባቡ በማጣራት ለህዝብ ግልፅ ለማድረግ በማይቻልበት፣ የህግ በላይነት እየተጣሰ፣ የዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ማዳን የማይችል መንግስትና ስርዓት ወደ መሆን ተሸጋግረዋል ማለት ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማስቆምና ለመግታትም ዋና ተግባሩ ያላደረገና ቁርጠኝነትም የሌለው ሆኗል።

የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ወደ ጎን በመተው ሌላ ጉዳይ ላይ በማትኮር የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ወደ ከፍተኛ ድቀትና ማሽቆልቆል እየገባ ነው። የአገሪቱ ልማት የሚመራውና የሚደግፈው አጥቶ፣ ልማታዊ አቅሞች እየመከነ፣ ስራ አጥነት እየተባባሰ፣ የህዝብ ኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰማይ የሚሰቀልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ምክንያትም ችግር በችግር ችግር እየተመሰቃቀለና እየተደራረበ በመሄድ ላይ ይገኛል። የህዝባችን ዋስትና የሆነው ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓታችን በማፍረስ አሃዳዊ ስርዓትን መልሶ ለመትከል እየሰራ ያለውና በዋናነት ይህንን አደጋና ጥፋት እየፈጠረና እየመራ የሚገኘው ትምክህተኛው ሀይልና በዙርያው የተሰባሰበ ፀረ ህዝብ ሐይል ነው።

በውስጣቸው ያለውን ድክመትና ፀረ-ህዝብ ተግባር ከመፍታትና ከማጥራት ይልቅ የሁሉም ችግር “ሶስተኛ ወገን አለው” የሚል የቆየ ዘፈን ሲደጋግሙ እየታየ ነው፡፡ ለአማራ ህዝብ የማይመለከተውና ያልተገባ ምስል እያስያዙና “ትምክህተኛ ተብለሃል!” እያሉ በዚህ ተሸፋፍነው በህዝቦች መካከል የቆየውን ዝምድናና ወንደማማችነት ለማደፍረስ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ህዝብ ትምክህተኞችን ታግሎ በእኩልነት የሚኖርባት አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት የማይተካ ሚና የተጫወተ ህዝብ ነው፡፡ የትግራይና የአማራ ህዝቦች በጋራ ትግላቸው ትምክህተኛውን አሸንፈዋል፡፡ ለወደፊትም ቢሆን እነዚህ ህዝብ ለህዝብ አጋጭተው እንዲባላ በማድረግ መኖር የሚፈልጉና ሓላፊነታቸውን ትተው ለጥፋት የተሰማሩ ሓይሎች በተደራጀ መንገድ ሊታገላቸው ይገባል፡፡

መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ከማንኛውም ጊዜ በላይ አገራችንን ለማዳን ሊረባረብ ይገባል፡፡ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሓይሎች የጀመራችሁትን ትግልና ሰፊ ትብብር መድረኮች አማራጭ የሌለው መሆኑን ተገንዝባችሁ ትግላችሁን አጠናክራችሁ ልትቀጥሉበት ይገባል፡፡ ህወሓትም የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ሕገ-መንግስት፣ ሰላምና የህዝቦችና የአገርን ደሕንነት በመጠበቅ የላቀ ሓላፊነት ያለብህ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፤ አገራችን እያጋጠማት ያለውን አደጋ በሚገባ ተገንዝበህ ከጥፋት ለማዳን እያደረገው ያለው ርብርብ፣ ለዚች ልዩ ታሪክና ክብር ያላት ሃገር ሉኣላዊነቷንና ሰላሟን በመጠበቅ ረገድ ዛሬም እንደወትሮ በላቀ ደረጃ ህዝባዊ ሓላፊነትህን ተቋማዊ እንድትህን አጠናክረህ በምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም የትግራይ ህዝብና ህወሓት ከጎንህ ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚፈፅሙ ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡

በህገ- መንግስቱ መሰረት ስድስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት የግድ መካሄድ ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ምርጫው በወቅቱ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ አቋማቸውን እየገለፁ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫው ለማካሄድ የሚያስችል ምንም ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ አይደለም፡፡ “በቂ ዝግጅት አላደረግንም” ተብሎ ምርጫውን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖሮው አይችልም፡፡ በአገራችን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነፃ የመወዳደር ዕድል አግኝተው ህዝብ በነፃ ፍላጎቱ የሚመርጠውን መንግስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ በህዝብ ፍፁም ፈቃድ በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ህገ-መንግስታዊ መብት በጥብቅ መከበር አለበት፡፡ ይህ በማይሆንበት ወቅት መላው የአገራችን ህዝቦች መብታችሁንና ሕገ-መንግስታዊ ስልጣናችሁን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን አውቃችሁ የላቀ ትግል ልታደርጉ በሚጠይቅ አስገዳጅ ጊዜ ላይ እንገኛለን።

የማንሻገረው ፈተና አይኖርም

ዘልአለማዊ ክብርና መጎስ ለስማእቶቻችን!

የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ

ጥቅምት 4/ 2012 ዓ/ም

መቐለ

Report Page