#eth

#eth


የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ጃዋር መሀመድ በመንግሥት ተመድበውለት የነበሩት የደህንነት ጥበቃ አባላት በምሽት እንዲነሱብኝ ታዘዋል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፈው መልዕክት ቁጣና ተቃውሞን ቀሰቀሰ።

በዚህም ሳቢያ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፎች ያጋጠሙ ሲሆን በርካታ ወጣቶችም ድርጊቱን በመቃወም አዲስ አበባ በሚገኘው የጃዋር መሀመድ ቤት አቅራቢያ ተሰብስበዋል።

የጸጥታ ኃይሎችም በአካባቢው ተሰማርተው እንዳሉ የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽር እንደሻው ጣሰው ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ቀርበው እንደተናገሩት በማንኛውም ፖሊስ የተወሰደ እርምጃ የለም። አቶ ጃዋር ተወሰደብኝ ያሉት ርምጃም ስህተት ነው ያሉ ሲሆን ፖሊስ መደበኛ ስራውን እየሰራ ነው ብለዋል ።

የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱና መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቀጥሉ ጥሪ ያስተላለፉ ሲሆን ፖሊስ የሕግ ማስከበር ሥራውን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ጃዋር እንደሚለው ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት አቅራቢያ ሁለት መኪኖች ወደሚኖርበት ቤት አካባቢ በመምጣት ጥበቃዎቹን "እኔ ሳላውቅ እቃቸውን ይዘው ቤቱን ለቀው እንዲወጡ" እንደተነገራቸው በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አስፍሯል።

አክሎም ጥበቃዎቹ ለምን እንዲወጡ እንደጠየቁና ለስልጠና እንደሆነ እንደተነገራቸው እነሱም እንዳልተቀበሉ፣ ከዚያም ስልክ ተደውሎላቸው በአስቸኳይ ቤቱን ለቀው ካልወጡ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ጠቅሷል።

በጥበቃዎቹ ላይ ግፊቱ ሲበረታ ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ሁኔታውን እንደነገሩትና እሱም ወደ አዛዡ ጋር ደውሎ ማብራሪያ እንደጠየቀና በመጀመሪያ ላይ "የተለመደው ጥበቃዎችን የመቀየር ሂደት መሆኑን" እንደተነገረው፤ ከዚያም ኃላፊው የተሰጠውን ትዕዛዝ ብቻ እያስፈጸመ መሆኑን ጽፏል።

ጃዋር ቀጥሎም ጉዳዩን የበለጠ ለማወቅ ከፖለቲካና ከጸጥታ አመራሮች ጋር መነጋገሩን እነሱም የተከሰተውን ነገር ከስር መሰረቱ ለማወቅ ቃል እንደገቡለት ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ በቤቱ አካባቢ በርካታ ደጋፊዎቹ መሰብሰባቸውንና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በጃዋር ላይ የሚገጥሙ ማንኛውንም ነገሮች በመቃወም ሰልፎች እየተካሄዱ ነው።

በአንዳንድ ቦታዎችም መንገዶች መዘጋታቸውንና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መገታቱን በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የሚገልጹ ሰዎች በፎቶ ጭምር እያመለከቱ ነው።

BBC

Report Page