#ETH

#ETH


የወላይታ ዞን አስተዳደር በወቅታዊ ዞናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ወላይታ ሶዶ ጥቅምት 11/2012 ዓ.ም

የወላይታ ዞን አስተዳደር በወቅታዊ ዞናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ በዞናዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዞኑ ለሚገኙ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው በሰጡት መግለጫ እንደተገለጸው በዞኑ በስፋት የሚታየውን ሥራ አጥነት ለማስወገድ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዞኑ የተጀመረውን የኢንዱስትሪ አብዮት ለመደገፍ በአንድ ጀምበር ከመንግሥታዊ መዋቅሮች ብቻ 136 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ አብዮቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማስቻል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚቀጥልም አቶ ዳጋቶ ገልጸዋል፡፡

ነገ የተሻለች ወላይታን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ሁሉም ኢንቨስተር የወላይታ ዞንን ተመራጭ አካባቢ የሚያደርግበት ዋናው ምክንያት አካባቢው ሰላምና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን በመገንዘብ ስለሆነ ህብረተሰቡ አሁንም የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት የሚፈልጉ ኢንቨስተሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ዳጋቶ በዞኑ ከ688 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ባለሀብቶች ያቀረቡት 22 ፕሮጀክቶች እንዲፀድቁ ተደርጓል፡፡

በህዝቡ ውስጥ ልማታዊ አስተሳሰብ የበላይነት የሚይዝበትን ሁኔታ በማረጋገጥ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና መልካም እሴቶችን ለማጎልበት የወላይታ ቴሌቪዥን ለማቋቋም መተዳደሪያ ደንብ እንዲፀድቅ ተደርጎ የቁሳቁስና የሰው ኃይል የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የወላይታ ባህል ማዕከል ግንባታ በተመለከተ ከዚህ ቀደም የተጠናው 3 ነጥብ 8 ሄክታር ቦታ ጠባብና የመሬት አቀማመጡ የማይመች ሆኖ ስለተገኘ ማራ ጫሬ ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ በመቀየር የዲዛይን ሥራ እንዲካሄድ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከሌዊ እስከ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ድረስ የሚዘልቀው መንታ የአስፋልት መንገድ ዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን አረጋግጠናል ያለው ዋና አስተዳዳሪው የመንገዱ ሥራ እስኪጀመር የሚያደርጉት ክትትል ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ከቀበሌ እስከ ዞን ድረስ ባሉት ምክር ቤቶች ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ከዛም በዞኑ ምክር ቤት ደረጃ ፀድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በጽሑፍ ከቀረበ በኋላ ለውሳኔ ሳይቀርብ እስካሁን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የዘገየው የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል በሚል በግንቦት 9/2011 ዓ.ም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱንና ወላይታን የወከሉ የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የዞንና የወረዳ አመራር አካላት በክልሉ ከፍተኛ አመራር መድረክ ከፍተኛ ትግል ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄን አስመልክቶ ከዞኑ ህዝብ ጋር ውይይት ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከዚህ ቀደም የተካሄደው ጉባኤ አስቸኳይ ነው በማለት አጀንዳው ከ48 ሰዓታት በፊት ስላልቀረበ ለውሳኔ አይቀርብም በሚል ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ አለመሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ሰሞኑን በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ጥያቄ አጀንዳ ተይዞ ለምክር ቤቱ እንዲቀርብና ውሳኔ እንዲሰጠው ከ48 ሰዓት ቀድሞ ህጋዊ ደብዳቤ የቀረበ ቢሆንም በክልሉ ምክር ቤት አጀንዳ አቅራቢ አስተባባሪ ደረጃ ይሁንታ ባለማግኘቱ አጀንዳው ሳይያዝ አልፏል ብለዋል፡፡

የወላይታ ህዝብ በክልል የመደራጀት ህገ መንግሥታዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ህገ መንግሥትንና የህግ የበላይነትን በጠበቀ መልኩ መሄድ እንዳለበት አቶ ዳጋቶ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Report Page