#ETH

#ETH


የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያው ሩብ አመት አፈጻጸሙ ከወንጀል ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በርካታ ንብረቶች በፍርድ ቤትና ከፍርድ ቤት ውጭ (በጉምሩክ ባለሰልጣን መ/ቤት) ለመንግስት ገቢ መደረጋቸውን በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ገለጹ፡፡

እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ በልዩ ሁኔታ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተወረሰ ንብረት በተመለከተ፤ በህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ወንጀል በፍትሃብሄር መቅጫ ስነ-ስርዓት ቁጥር 266815 መሰረት 3,631,140.00 የአሜሪካን ዶላር እና 3,5000000 የኢትዮጵያ ብር፤ ወደ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ እንዲሁም ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ካዝና ፈሰስ የተደረገ ሲሆን፤ በህግ ውርስ ከተደረገ ገንዘብና ንብረት ጋር ተያይዞም 27‚755.00 የአሜሪካ ዶላር፣ 66944.00 ዩሮ፣ 2‚985.00 ዴርሀም፣ እንዲሁም 16,185.00 ፓውንድ ፣15,500 .00 ሪያድ፣ ፣22,450.00 የስዊዝ ፌራንክ እና 100.00 ናቅፋ (የኤርትራ ብር) ወደ መንግስት ካዝና ገቢ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በህግ ውርስ የተደረገ ንብረትን አስመልከቶ ከጦር መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ 4 ከባድ መትረየስ፣ 42 ክላሽ፣ 1 ማካሮቭ፣ 20‚996 የተለያዩ አይነት ጥይት፣ 27 ካዝና፣ እንዲሁም 10‚676 የክላሽና የሽጉጥ ጥይት፣ 1 ባለሰደፍ ክላሽ ፣ 6 ሽጉጥ፣ በአቃቤ ህግ ውሳኔና በጉሙርክ አዋጅ በአጠቃላይ በቀረቡ 8 ክሶች መነሻ የሁሉም ተከሳሾች የዋስትና መብት ታግዶ ጉዳያቸው በህግ እየታየ ህግና ስርዓትን ተከትሎ እንድወረሱ ለፖሊስ አቅጣጫ መሰጠቱን አቶ ዝናቡ አብራርተዋል፡፡

ከማዕድን ጋር በተያያዘ 17.3 ኪሎ ግራም ብር ብሎም የቀረጥና የታክስ መጠኑ 250 ሺህ ብር የሆነ የብር ጌጣጌጥ ፣ የዋጋ ግምቱ 18 ሚሊዮን ብር የሆነ 8.75 ኪሎ ግራም ወርቅ፣ በዐቃቤ ህግ ውሳኔና በጉሙርክ አዋጁ መሰረት በአይነት ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉ ተገልጿል፡፡

አጠቃሊይ የዋጋ ግምታቸው 733 ሺህ የሚጠጋ መድሃኒት፣ ፍላሽ፣ ጫማና አልባሳት፣እንዲሁም አርቴፌሻል ዊግ እና የለስላሳ መጠጦች የሚወገዱና በጉምሩክ ህግና የአሰራር ስርዓት አግባብ መሰረት ወደ ገንዘብ እንዲቀየሩ ለጉሙርክ ተላልፈዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከከባድ መኪና ውርስ ጋር በተያያዘ 3 (ሶስት) አይሱዙ መኪና እንዲሁም፣ ራቫ ፍር መኪና ሻግ ተሰርቶባቸው የጦር መሳሪያ ሲያጓጉዝ በመያዛቸው ውርስ እንዲደረጉ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን አይሱዙ የጭነት መኪናው በሀሰተኛ ሰነድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በመያዙ ውርስ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም አቶ ዝናቡ ከምግብ ዘይቶችና ከልባሽ ጨርቆች እንዲሁም ከብና እና ከሽሻ ዝውውሮች ጋር ተያይዞ ተመሳሳይ ተግባራት ተፈጽመው በህጉ መሰረት ውርስ መደረጋቸውን ገልጸው ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነትና መሰል ተግባራት ሲፈጸሙ ካየ ለፍትህ አካላት ጥቆማዎችን በመስጠት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ በመቀነስ ደረጃ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

FDRE Attorney General የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

Report Page