#ETH

#ETH


የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት አገልግሎት ለመስጠት 14 ድርጅቶች ፈቃድ ጠየቁ!


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ወር በፊት ይፋ ያደረገውን የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ስምሪት (ኤታስ) መመሪያ ተከትሎ አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩ እንዲሁም አዳዲስ 14 ድርጅቶች ፈቃድ ለማግኘት አመለከቱ።

ካመለከቱት ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት በድምፅ፣ በመተግበሪያዎች እና በአጭር የጽሑፍ መልዕክት አማካኝነት አገልግሎቱን ለመስጠት ማመልከታቸውን በባለሥልጣኑ የፈቃድ አሰጣጥ የሥራ ኀላፊ የሆኑት አልአዛር ይርዳው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። እንደ ኀላፊው ገለጻ፤ አገልግሎቱን ለመስጠት ጥያቄውን ያቀረቡትን ድርጅቶች ከመመሪያው አንፃር እየመረመሩ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥም ፍቃዱን ለመስጠት የሚያስፈልገውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው ይፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ባካሔደው ጥናትም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ነገር ግን ለምዝገባ ወደ ተቋሙ ያልመጡ ስምሪት ሰጪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ‹‹የኤሌክትሮኒክ ስምሪቱ ለታክሲ ብቻ ሳይሆን ለከተማው የሕዝብ ትራንስፖርት ስምሪትም ጠቃሚ ሆኖ በመገኘቱ ጥቅም ላይ ለማዋል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አሉ›› ሲሉ አልአዛር ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ 17 ሺሕ 694 ተሸከርካሪዎች እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከባለሥልጣኑ ያገኘችው መረጃ ያሳያል። ኮድ ሦስት ሚኒባስ ታክሲዎች ከሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር በመያዝ 8 ሺሕ 607 ናቸው። ኮድ አንድ ሚኒባስ ታክሲዎች 5 ሺሕ 661 ሲሆኑ 637 አንበሳ አውቶብሶች ይገኛሉ። ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት 4 መቶ ተሽከርካሪዎች ሲኖሩት አንድ መቶ የተማሪ ሰርቪሶች ይገኛሉ። አይሲውዙ ቅጥቅጥ 376፣ ፐብሊክ ሰርቪስ 192 እንዲሁም 418 ሃይገር ሚኒባስ ታክሲዎች አሉ።

ማንኛውም የኤታስ አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ ሰው አንድ ቁጥር ታርጋ ማውጣት የሚጠበቅበት ሲሆን ስምሪቱን አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ውል መዋዋል አገልግሎቱን ለማግኘት ከሚጠበቁ መስፈርቶች መካከል አንዱ ነው። የስምሪት አገልግሎቱን የሚሰጡት ድርጅቶችም የመረጃ ቋትን ጨምሮ የተለያዩ የአገልግሎት መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

ቮልስ ዋገን ባሳለፍነው ሳምንት በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ወደ ሥራ ያስገባውን የኤታስ አገልግሎት ባስተዋወቀበት ወቅት ገበያውን ወደ ኢትዮጵያ እና ጋና የማስፋፋት እቅድ እንዳለው ይፋ አድርጓል። እንደ ቮልስ ያሉ የመኪና አምራቾች ከአሽከርካሪዎች ጋር በሚገቡት ውል ተሸከርካሪውን ካቀረቡ በኋላ የስምሪት አገልግሎቱንም ጨምረው ይሠራሉ።

ቮልስ በሩዋንዳ በ 20 ሚሊዮን ዶላር የመኪና መገጣጠሚያ በማስገንባት ወደ ሥራ የገባ ሲሆን በድርጅቱ ባለቤትነት ከአንድ እስከ ኹለት ዓመት በመኪኖቹ ከተጠቀመ በኋላ ባገለገሉ መኪኖች ዋጋ ወደ ገበያ እንደሚያወጣውም ኢንዲፔንዳንት ዘግቧል።

የኤታስ ድርጅቶች ፈቃድ አግኝተው ሕጋዊ ሰውነታቸውን ባለሥልጣኑ ከተቀበለ በኋላም፣ አገልግሎት ሰጪዎችን መመዝገብ እንደሚችሉ መመሪያው ይደነግጋል። ነሐሴ 24 ቀን 2011 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው መመሪያው፣ ማንኛውም የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በአንድ ዓመት ውስጥ ምዝገባውን መጨረስ እንደሚገባው ባለሥልጣኑ ማስታወቁ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ተገድቦ የሚገኘው የኤታስ አገልግሎት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ያቃልላል የሚል ግምት ቢኖርም የሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚታዩ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሰዋል ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ኤታስ አሽከርካሪዎች እንደሚሉትም ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መመጣጠን እየታየ መምጣቱን ይናገራሉ። ነገር ግን በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውረው ለመሥራት እንደሚቸገሩ እና ይህም ስምሪቱ መሔድ የሚችለውን ያህል እንዳይሔድ አድርጎታል ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

‹‹በተለይም ከከተማ እየራቅን በሔድን ቁጥር የሚደርስብን ጥቃት ይጨምራል፣ ይህም አላግባብ ትርፍ መሰብሰብ በለመዱ የላዳ ታክሲ ሹፌሮች ድብደባ እና መኪኖቻችን ላይም የተለያዩ ጉዳቶች ይደርሱብናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ምንጭ፦ አዲስ ማለዳ

Report Page