#ETH

#ETH


ዓለም ዐቀፉ የጉምሩክ ድርጅት በየአምስት ዓመቱ የሚያሻሽለውን የታሪፍ መጽሐፍ መሰረት በማድረግ ከኹለት ዓመት በፊት ተከልሶ መጠናቀቅ ይገባው የነበረውን የታሪፍ መፅሐፍ በማዘጋጀት ያፀደቀው የገንዘብ ሚኒስቴር አዳዲስ መኪኖች ላይ የአምስት በመቶ የቀረጥ ቅናሽ አደረገ።

የታሪፍ መጽሐፉ ለተሽከርካሪ ምርቶች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እና ከዚህ ቀደም ከሦስት ገፅ ባልበለጠ የተዘረዘረውን ሰንጠረዥ ከ 34 ገፅ በላይ ከፍ በማድረግ አሻሽሏል። የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር እና የትራንስፖርት ባለሥልጣን በጋራ በመሆን ከአንድ ዓመት በላይ በፈጀ ጊዜ ባካሔዱት ጥናት መሰረት የታሪፍ መጽሐፉ ዝርዝር መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል።

በተሸከርካሪ ላይ ከተደረጉት ማስተካከያዎች መካከል አንዱ ከአስር ዓመት በላይ እና በታች በመለየት በመጽሐፉ ላይ ለኹለት መከፈሉ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት እስከ አስር ዓመት ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችም በየዓመቱ የተከፋፈሉበት ነው። ምንም እንኳን ከአንድ ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ተመሳሳይ 35 በመቶ ቀረጥ ቢጣልባቸውም ወደፊት በሚወጡ ሕጎች መሰረት በዓመት በተከፋፈሉት ተሽከርካሪዎች ላይ ሕግ አውጪው የተለያዩ ቅጣቶችን ሊጥል እንደሚችልም ተጠቁሟል።

የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማበረታታት በሚልም በተለይም ሙሉ በሙሉ ተበትነው የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ያደረገ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ መኪናን በዝርዝር ውስጥ በማካተት ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ ፈቅዷል። የኤሌክትሪክ እና የነዳጅ ኀይል ቀላቅለው የሚጠቀሙ መኪኖችም በመጽሐፉ የተካተቱ ሲሆን የተጣለባቸውም ቀረጥ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን እና የአየር ንብረት ብክለትን ለመቋቋም እንዲሁም የነዳጅ ፍጆታን ለመቀነስ በሚል በተደረገው ጥናት መሰረት መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የመኪና አምራቾች እንደሚሉት፣ የተደረገው የቀረጥ ቅናሽ በተለይም ሙሉ በሙሉ ያልተገጣጠመ መኪና ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች አበረታች ነው። ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያሉ ገጣጣሚዎች በከፊል የተገጣጠመ መኪና የሚያመርቱ ሲሆን በከፊል የተገጣጠመ ይባል እንጂ የሚገጣጥሙበት ደረጃ ይለያያል።

‹‹ሙሉ ለሙሉ ያልተገጣጠመ ተሸከርካሪ ማምረቻ ለመክፈት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የገበያው ስፋት ይወስነዋል›› ሲሉ የማራቶን ሞተር ዋና ሥራ አስኪያጅ መልካሙ ይናገራሉ። ‹‹ማራቶን ሞተር በምሥራቅ አፍሪካ ዘመናዊ የተባለለትን መገጣጠሚያ ይዞ ቢሠራም በከፊል በመገጣጠም ስም ግን የተለያዩ ዓይነት ደረጃ ያላቸው ፋብሪካዎች አሉ። በእኛ አገር ገበያ አቅም ሙሉ በሙሉ ያልተገጣጠመ መኪና ፋብሪካ ለመክፈት የገበያው አቅም ባይፈቅድም ወደ ውጪ ለመላክ በማሰብ የተወሰኑ ፋብሪካዎች ሊመጡ ይቻላሉ፣ ከብራንድ ጋር የሚነሱ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው። በተለይም እናት ድርጅቶች በሃገር ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ጋር ጥምረት በመፍጠር ወደ ሥራ ለመግባት በሚያበረታታ መልኩ ነው አዲሱ የታሪፍ መጽሐፍ የፀደቀው።›› ብለዋል።

አዲስ መኪና ማለት ከተመረተ ጀምሮ ምንም አይነት አገልገሎት ያልሰጠ ወይም ከአንድ ዓመት በታች ያገለገለ መኪና ማለት አንደሆነ የታሪፍ መጽሐፉ ደንግጓል።

በታሪፍ መጽሐፉ ላይ ከመጡ ለውጦች መካከል ኹለተኛ መደብ ስር የነበሩ ከ 1ሺሕ አምስት መቶ በላይ ዝርዝሮችን ወደ አምስት መቶ ማሳነሱ አንዱ ነው። ኹለተኛ መደብ የሚባለው እና ማበረታቻ የሚሰጥባቸው ሸቀጦች ሲሆኑ በዚህ መደብ ለመስተናገድም የምስክር ወረቀትን ጨምሮ የተለያዩ መስፈርቶችን በመደርደር በአገልግሎት ሰጪው ላይ የአስተዳደር ጫና የሚያሳድር እና በተገልጋዮች ላይም አላስፈላጊ መጉላላት የሚያስከትል እንደነበር በጉምሩክ ኮሚሽን የታሪፍ ምደባና ስሪት አገር አወሳሰን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጌቱ ለገሰ ይናገራሉ።

በአንደኛ መደብ ውስጥ የተካተቱት አገልግሎቶች እንደማንኛውም ዓይነት ንግድ ፈቃድ እንዳለው ተገልጋይ የሚስተናገዱ ይሆናል ሲሉ ኀላፊው ተናግረዋል።

ዓለም ዐቀፉ የጉምሩክ ድርጅት በየአምስት ዓመቱ የታሪፍ መጽሐፍ የሚያትም ሲሆን የድርጅቱ አባል ሃገራትም አዲስ የታሪፍ መጽሐፍ ሲታተም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የታሪፍ መጽሐፋቸውን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል። ከኹለት ዓመት ተኩል በኋላ አዲስ የታሪፍ ኮድ የሚወጣ ሲሆን በጉምሩክ የሚመለከታቸው አካላትም በድጋሚ መዘግየት እንዳያጋጥም ከወዲሁ ዝግጅት መጀመራቸውን ጌቱ ተናግረዋል።

የታሪፍ መጽሐፍ ማለት በዓለም ዐቀፉ የጉምሩክ ተቋም የሚዘጋጀውን እና የሸቀጦች መለያ የሆነውን እንዲሁም አያንዳንዱ እቃ በዓለም ዐቀፍ ገበያ ያለውን መለያ ቁጥር እንዲሁም ቀረጥን የሚያካትት ነው።

ከተሸከርካሪ ባሻገርም በቴሌቪዥን እና በማቀዝቀዣ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለሚገጣጥሙ ድርጅቶች የቀረጥ ቅናሽ የተደረገ ሲሆን ከዚህ ቀደም ተገጣጥሞ ያለቀ እንዲሁም በሃገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ቢሆኑም ተመሳሳይ ቀረጥ መጠን ሲጣልባቸው እንደነበረም ለማወቅ ተችሏል።

‹‹ሰነዱ ለሚመለከታቸው ተቋማት ተበትኖ ሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን መመሪያው ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተጫኑ እቃዎች ግን በቀድሞው መመሪያ መሰረት እየተስተናገዱ ይገኛል›› ሲሉ ጌቱ ተናግረዋል።

Via ADDIS MALEDA

Report Page