#ETH

#ETH


የትግራይ ክልል አዲስ ገቢ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ወደ አማራ ክልል ላለመላክ ስለያዘው አቋም፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየተነጋገረ መሆኑ ተገለጸ፡፡ የውይይቱ ውጤትም በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ክልሉ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ መሆኑን በመጥቀስ ነው፣ ወደ አማራ ክልል ተማሪዎችን እንደማይልክ ያስታወቀው፡፡ በዚህ ዓመት 9,000 የትግራይ ተወላጆች ወደ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል የሚያስችላቸውን ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ አማራ ክልል ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ የተመደቡት 2,000 እንደነበሩ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመወያየት ቁጥራቸው ወደ 600 ዝቅ እንዲል መደረጉን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ገብረ መስቀል ካህሳይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር 40 በመቶ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በክልላቸው እንደሚመደቡ፣ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ተለያዩ ክልሎች ይላኩ እንደነበር ገልጸው፣ ብሔርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በበዙበት በዚህ ወቅት ግን ይህ ተቀይሮ በክልላቸው የሚመደቡ ተማሪዎች መጠን ወደ አሥር በመቶ ዝቅ ማለቱን ወደ ሌሎች ክልሎች የሚደለደሉት ደግሞ ወደ 90 በመቶ ከፍ ማድረጉ ተገቢ አይደለም ብለዋል ኃላፊው፡፡

በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ የተመደቡት 600 ተማሪዎች ሌላ ቦታ እንዲመደቡ እንደሚሠራ፣ ይህ ካልሆነ ግን የትግራይ ክልል ሌላ አማራጭ ይፈልጋል የሚል አቋም መያዙን ገብረ መስቀል (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በመርህ ደረጃ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የክልል መንግሥታት መቆጣጠር የሚችሉት በቋንቋቸው የሚሠሩባቸውን የመምህራን ማሠልጠኛና የግብርና ኮሌጆችን ነው፤›› ያሉት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ፣ ካለው የፀጥታ ሁኔታ በመነሳት ክልሉ የሰጠው መግለጫ አግባብነት ባይኖረውም አመራሮች ከክልሉ መንግሥት ጋር እየተወያዩበት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ደቻሳ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹን ላለመላክ የያዘው አቋም ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበት ዕድል ጠባብ መሆኑንም ለሪፖርተር ነግረዋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲዎች ለሆነ ክልል የሚያስቀሩት ትርፍ ቦታ የላቸውም፡፡ በጀት የሚመደብላቸውም በተማሪዎች ቁጥር ልክ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በውይይቱ የሚደረስበትን የመጨረሻ ውሳኔ ግን ከሰሞኑ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚታወቅ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ በሚገኙ 50 የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዚህ ዓመት 142,943 አዲስ ተማሪዎች እንዲገቡ ተደልድለዋል፡፡ የመጀመርያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በፍኖተ ካርታው መሠረት በማኅበራዊ ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ፣ በመምህርነት፣ በተፈጥሮ ሳይንስ መምህርነት በአራት መደቦች ተደልድለው የጋራ ኮርሶችን እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡

በሕግ፣ በሕክምና፣ በጥርስ ሕክምና፣ በእንስሳት ሕክምናና በኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ የሚመደቡ ተማሪዎች የጋራ ኮርሶቹን የሚወስዱት ለአንድ ሴሚስተር ሲሆን፣ የተቀሩት ግን የመጀመርያውን ዓመት ሙሉ የትምህርት መርሐ ግብር የጋራ ኮርሶችን እንደሚወስዱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ፍኖተ ካርታው የተማሪዎች ዝቅተኛው የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ጊዜን ወደ አራት ዓመትም ከፍ አድርጓል፡፡  

Via ሪፖርተር

Report Page